ቀጥታ፡

ገንዘብ ገበያ ላይ የሚቆይበት ጊዜ ገደብ ሊኖረው ይገባል- የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2010 የኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ ገበያ ላይ የሚቆይበት ጊዜ ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናገሩ። የመገበያያ ገንዘብ የጊዜ ገደብ አለመኖር ሀሰተኛ ገንዘቦችን ለማተምና በግለሰብ እጅ ገንዘብን እንዲያከማች ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ይህም እንደ አገር ኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ መገበያያ ገንዘብ ገበያ ላይ የሚቆይበት ጊዜ ገደብ ሊኖረው ይገባል ነው ያሉት። እንደ ባሙያዎቹ ገለጻ የገንዘብ ኖቶችን ለማተም የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ ነው። ይሁንና ገንዘብን ለረዥም ጊዜ ማቆየት በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በመረዳት የብር ኖቶችን በተለያዩ ወቅቶች መቀየር ይገባል ብለዋል። ዶክተር አሰፋ አድማሴ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር የአንድን ሀገር ገንዘብ ለማተም ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም ገንዘብ በገበያ ውስጥ የቆይታው ጊዜ በተራዘመ ቁጥር የመጭበርበር ማለት በተሳሳተ ገንዘብ መለወት እድሉ የሰፋ ስለሚሆን የመቆያ ጊዜ ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ ነው ያብራሩት፡፡ ብዙ አገሮች በየጊዜው ያሻሽላሉ ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይለውጡት የተወሰኑ ነገሮች ይጨመራሉ ይህም ኢኮኖሚው ውስጥ ሊደርስ የሚችለውን የማጭበርበር ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ ገንዘቡ ኖቱ ይቀደዳል፣ ገበያው ላይ የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን ይቀንሳል ፣ አንዳንድ ሰዎችም አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ገንዘባቸውን ይዘው ቁጭ የሚሉበት ሁኔታ አለ ፤  ስለዚህ ቢለወጥ ጥሩ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰትተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ በበኩላቸው "ሃሰተኛ ገንዘብ እንዳይታተም ሊያደርግ ይችላል፤ ሌላው የቆይታ ጊዜ ትልቁ ነገር ሰዎች በጣም በብዛት እንዳይዙ ይፈራሉ ምክንያቱም አሁን ዛሬ ኤክስፓየር የሚያደርግ ገንዘብ ሰው በሚሊዮን ይዞ ነገ ዜሮ ሊወጣ ነው ስለዚህ የቆይታ ጊዜ ካለ ሰው ስለሚሰጋ ብዙ ገንዘብ በእጁ ይዞ አይገኝም በዛ በኩል ሊረዳ ይችላል ነገር ግን አንዳንድ ግርታ የሚፈጥርበት ሁኔታም አለ ገንዘብ የቆይታ ጊዜ በሚኖረው ጊዜ በየጊዜው ገንዘቦችን ለማተም ከፍተኛ የሆነ ሎጀስቲክስ ነው የሚያስፈልገው። እንደ አስፈላጊነቱ በአዲስ ኖቶች ፕሪንት አድርጎ መተካት ይቻላል"ብለዋል፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው የብር ኖቶች ሊቀየሩ ይገባል ባይ ናቸው የሳንቲም 20 እና 50 ብር ያላቸው ሀገሮች እንዳሉ በመጥቀስ እኛ ሀገር መቆጣተሪያው ዘዴም ዝቅተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ በመሆኑም አደጋዎችን ለመቀነስ የብር ኖቶችን የመለወጥና አዳዲስ ኖቶችን የማዘጋጀት ስራዎች ሊታሰብበት እንደሚገባ ነው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ያሳሰቡት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም