ቀጥታ፡

የኩላሊት ህሙማን በመድሃኒት የዋጋ ንረት እና የአቅርቦት እጥረት እየተቸገሩ መሆኑን ተናገሩ

መጋቢት 28/2013/ኢዜአ/ የኩላሊት ህሙማን በመድሃኒት የዋጋ ንረት እና የአቅርቦት እጥረት እየተቸገሩ መሆኑን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በበኩሉ የመድሀኒት እጥረቱን በዘላቂነት ለመፍታት ከተለያዩ ሀገራት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ከህሙማኑ መካከል የኩላሊት እጥበት በማድረግ ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ አሊ ናስር እና አቶ ሰለሞን ደገባሳ ለኢዜአ እንደሚሉት እጥረትና ሲገኝም ውድነቱ ፈተና ሆኖባቸዋል።

በሳምንት ሶስት ጊዜ የኩላሊት እጥበት እየተደረገላቸው በመሆኑ በየጊዜው ዋጋ እየጨመረ የመጣውን የመድሃኒቱን ውድነት መቋቋም እንደተሳናቸውም ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት 110 ለሚሆኑ የኩላሊት ህሙማን ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የኩላሊት እጥበት ታካሚዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ሳቢያ የመድሃኒት እጥረቱ እየተባባሰ ስለመሆኑ ይገልፃሉ።

ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ቢያደርግም ብዙ መድሃኒቶችን ታካሚዎች በራሳቸው የሚገዙ በመሆኑ በመንግስት ሆስፒታሎች በ200 ብር የሚሸጥ መድሃኒት ከግል ተቋማት እስከ 1 ሺህ ብር ለመግዛት እንገደዳለን ብለዋል።

በመሆኑም የሚመለከተው የመንግስት አካል ለችግሩ ትኩረት በማድረግ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ሰሎሞን አሰፋ፤ የኩላሊት ህመምተኞች ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ የመድሃኒት እጥረቱን እንዳባባሰው ይናገራሉ።

የተወሰኑ ፋርማሲዎች ደግሞ ሆነ ብለው መድሃኒት በመደበቅ እጥረት እንዲከሰትና በደላሎች አማካኝነት በተጋነነ ዋጋ እንዲሸጥ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የግዢ አስተጸዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ በበኩላቸው ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የመድሃኒት አቅርቦት ችግር መከሰቱን አንስተዋል።

አሁን ላይ ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከተለያዩ ሀገሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከግዥ ጋር በተያያ ከ80 በመቶ በላይ መድሃኒቶች ከውጭ ስለሚመጡ አልፎ አልፎ እጥረት መኖሩንም አንስተዋል።

ሆኖም ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የተቀላጠፈ አሰራርና አቅርቦት እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።

መንግስትም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድሃኒቶች ከማካማቻ ቦታወች በፍጥነት እንድነሱና እንዲሰራጩ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት 50 እና 60 ቀናት ወደብ ላይ እና አየርመንገድ ከ1 ወር በላይ ይወስዱ የነበረን ጊዜ በአጭር ጊዜ እንዲነሱና እንዲከፋፈሉ ማድረግ ተጀምሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም