ቀጥታ፡

በምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

ባህርዳር፤ መጋቢት 28/2013 በስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ የባህር ዳር ልዩ ዞን የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪ አቶ መንግስቱ አማረ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዘንድሮው ምርጫ የሴቶችን ንቁ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ድርጅታቸው ጥረት እያደረገ ነው።

ለዚህም ፓርቲው ቀርጾ ባወረደው የምርጫ ስነ ምግባር መመሪያ አጠቃላይ በእጩነት ከሚቀርቡት ውስጥ ቢያንስ 30 በመቶ  ሴቶች እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጦ  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል  ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች እጩዎችን ሲያስመዘግብም በመመሪያው መሰረት ሴቶችን ለማሳተፍ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በእጩነት ከማስመዝገብ ባሻገር የሀገሪቱ ህዝብ ግማሽ ቁጥር ያላቸው ሁሉም ሴቶች የምርጫ ካርድ በማውጣት በመራጭነት ሙሉ ተሳትፏቸውን እንዲያረጋግጡ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

''ሴቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችንና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ምርጫ እንዲካሄድ ፓርቲያችን  እየሰራ ነው '' ያሉት ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ የባህር ዳርና አካባቢው ማስተባበሪያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አማረ ጌትነት ናቸው።

ከምርጫው ቀደም ብሎ ለሴቶች ተከታታይ ስልጠናና የአቅም ግንባታ በመስጠት ወደ አመራር እንዲመጡ እየሰራ ቢሆንም ድርጅቱ በሚፈልገው ደረጃ ተሳትፏቸው ማደግ አለመቻሉን ተናግረዋል።

ለዚህም እስካሁን የተመጣበት አካሄድ በግፍ፣ በደልና ጭቆና ላይ የተመሰረተ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህን መሰረታዊ ችግር ለማቃለል አብን ከአቅም ግንባታ ጎን ለጎን  በእኩልነትና ተጠያቂነት መርህ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት በመገንባት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ /አዴሃን/ ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው ድርጅታቸው በኤርትራ በረሃ በትጥቅ ትግል በነበረበት ወቅት ጀምሮ በሴቶች እኩልነትና ተሳትፎ የማይደራደር ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ በረሃ የገባውም በአማራ ህዝብ ላይ በሃሰት ትርክት ተመስርቶ ይፈጸም በነበረው ግፍና በደል የሴቶች ተጠቂነት የበለጠ በመሆኑ የተዘጋውን የዴሞክራሲ በር ለማስከፈት ያለመ ነበር ብለዋል።

መንግስት ባደረገው ጥሪ ወደ ሀገር ከገቡ በኋላም በሰላማዊ መንገድ በምርጫ አሸንፈው ወደ ስልጣን ለመውጣት ትግል ሲጀምሩ ለሴቶች ተሳትፎ ቅድሚያ ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀረጹት የምርጫ ማኒፌስቶ ለሴቶች የእኩልነት ተሳትፎና መብት መረጋገጥ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን አሰረድተዋል።

በዘንድሮው ምርጫ ሴቶች በእጩነት፣ በመራጭነት፣ በአስመራጭነትና በታዛቢነት በንቃት በመሳተፍ በዴሞክራሲያዊ የመንግስት ምስረታው የእኩልነት መብታቸውን እንዲያረጋግጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማገዝ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማበብ ፓርቲው የድርሻውን እንደሚወጣ  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም