“ብሔራዊ ቡድኑ ያደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች በአፍሪካ ዋንጫ ለነበረው ጉዞ ጉልህ ድርሻ ነበረው”...አሰልጣኝ ውበቱ አባተ - ኢዜአ አማርኛ
“ብሔራዊ ቡድኑ ያደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች በአፍሪካ ዋንጫ ለነበረው ጉዞ ጉልህ ድርሻ ነበረው”...አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ከአፍሪካ አገራት ጋር ማድረጉ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላደረገው መልካም ጉዞ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ገለጸ።
በካሜሮን አስተናጋጅነት በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በምድብ ዘጠኝ የነበረችው ኢትዮጵያ ኮትዲቫዋርን ተከትላ በውድድሩ ላይ መሳተፏን አረጋግጣለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ቀደም ባለው ጊዜ የወዳጅነት ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ያደረግ የነበረው አገር ውስጥ ካሉ ክለቦች ጋር ነበር ያለው አሰልጣኝ ውበቱ ፤ ከአፍሪካ አገራት ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጉ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ጉልህ ሚና እንደነበረው ገልጿል።
በተጨማሪም ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ተጫዋቾች ቀድመው ተጠርተው ዝግጅት መደረጉ ለውጤቱ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብሏል።
በአጭር ጊዜ ቡድኑን ማዘጋጀት ከባድ እንደነበርና ያም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች መታየታቸውንና በተለይም "ጎል አስቆጣሪ ቡድን" መስራት እንደተቻለ አመልክቷል።
በቀጣይም ክለቦችን በማይጎዳ መልኩ ተጫዋቾችን ቀድሞ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግና ከክለቦች አሰልጣኞች ጋር በብሔራዊ ቡድኑ በሚመረጡ ተጫዋቾች ላይ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል።
እ.አ.አ በ2022 በኳታር በሚካሄደው 22ኛው ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ አገራት የማጣሪያ ጨዋታ በምድብ ሰባት ኢትዮጵያ ከጋና፣ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ ጋር ተደልድላለች።
የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ለሚያደርገው ዝግጅት እግረ መንገዱን አቋሙን የሚፈትሽበት እንደሆነ አሰልጣኝ ውበቱ ተናግሯል።
በተለይም ኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ጋናና ዚምባቡዌ በአፍሪካ ዋንጫ ጭምር ተሳታፊ መሆናቸው ለቡድኑ እንደ ጥሩ እድል የሚታይ ነው ብሏል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም በምታስተናግደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ(ሴካፋ) ከ23 ዓመት በታች ውድድር ታዳጊ ተጫዋቾችን እንደሚያሰልፍ ነው አሰልጣኝ ውበቱ የገለጸው።
ዋናው ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እንደሚዘጋጅ አመልክቷል።
ይሄ ውሳኔ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ የጨዋታ መደራረብ ጫና እንዳይፈጥርና ለታዳጊ ወጣቶች እድል መስጠትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ የካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ለ11ኛ ጊዜ ሲሆን ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው እ.አ.አ በ2013 ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።