የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

85
ሰመራ ሀምሌ 23/2010 የአፋር ብሔራዊ ከልላዊ መንግስት ምክር ቤት ለ2011 በጀት ዓመት ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ። ምክር ቤቱ በ3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤው የአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሹመትንም አጽድቋል። ላለፉት ሁለት ቀናት በሰመራ ከተማ ሲካሄድ ቆየው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በክልሉ የ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት የአስፈጻሚ አካላት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ጨምሮ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ አጽድቋል። የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን መቅቡል ለ2011 በጀት ዓመት በክልሉ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ማስፈጻሚያ የሚውል ከ5 ቢሊዮን 157 ሚሊዮን ብር በላይ ረቂቅ በጀት ለምክር ቤቱ እንዲጸድቅ አቅርበዋል። በእዚህ ወቅት እንዳሉት በጀቱ የ2010 ዓ.ም የሥራ አፋጻጸምንና የሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው። በጀቱ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ በ14 በመቶ እድገት ያለው ሲሆን የበጀት ምንጩም ከፌዴራል መንግስት ግምጃ ቤት፣ ክልሉ ገቢና ከውጭ እርዳታ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል። በጀቱ በክልሉ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ-ልማቶችን ለማስፋፋትና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ እንዲሁም ተያያዥ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል መሆኑንም አቶ ኡስማን አያይዘው ገልጸዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ የፍትህ አገልገሎት ለመስጠት በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን ብቃት በለው የሰው ኃይል ለማደራጀት የጀመረውን ሥራ ለማገዝም የአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሹመት በክልሉ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ለምክር ቤቱ ቀርቦ ምክር ቤቱ ሹመቱን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም