ቀጥታ፡

የሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምቹ ፖሊሲዎችን ቀርጾ መተግበር ያስፈልጋል...ጥናት

መጋቢት 26/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሥነ- ሕዝባዊ ትሩፋት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የልማት ስራዎችን ማጠናከርና ምቹ ፖሊሲዎችን ቀርጻ መተግበር እንዳለባት አንድ ጥናት አመለከተ።

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ትብብር የተጠና ጥናት እንዳመለከተው የሥነ- ሕዝባዊ ትሩፋት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጅምር የልማት እንቅስቃሴዎችን ማጠናከርና ምቹ ፖሊሲዎችን ቀርጾ መተግበር ይገባል።

ጥናቱ ኢትዮጵያ የእድሜ አወቃቀር ሽግግርን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ፈጣን የምጣኔ ሃብት እድገት እውን ለማድረግ በሚያስችላት አመቺ የልማት ጉዞ ላይ መሆኗን አመላክቷል።

ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት በሕዝብ የእድሜ አወቃቀር ለውጥ ፣ በሰራተኛ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች (15-64 ዓመት) ቁጥር ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታችና ከ64 ዓመት በላይ ከሆኑ ሰዎች ቁጥር በልጦ ሲገኝ የሚፈጠር የእድገት ዕድል መሰረት ነው፡፡

የዚህን በጊዜ የተገደበ ዕድል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ አሰራር እንደሚያስፈልግ ጥናቱ ጠቁሟል።

በጤና፣ በትምህርት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሴቶች ተጠቃሚነትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የተጠናከረ ስራ ማከናወንና ምቹ ፖሊሲዎችን መቅረጽ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጥናቱ አስቀምጧል፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በተለይ በህጻናትና እናቶች ጤና አበረታች ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።

በተጨማሪም በቤተሰብ ምጣኔ፣ በትምህርት በተለይ በልጆችና ልጃገረዶች የትምህርት ተሳትፎ የተሰጠው ትኩረት አዎንታዊ ውጤትን እያስመዘገበች እንደምትገኝ አስቀምጧል፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለውን ከፍተኛ ቁጥር ያለውነ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በተለይ ደግሞ ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች ማሰልጠንና ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ መክሯል።

ለዚህም ጠቃሚና ምርታማ በሆኑ የሥራ ዘርፎች ላይ ማሰማራት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ቀርጾ መተግበር ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን በተገቢው መልኩ ዕውን ለማድረግ ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን ጥናቱ አስገንዝቧል፡፡

ጥናቱ የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊሲካል ፖሊሲዎች ትግበራ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን በሚያጎለብቱና ከፍተኛ የሰው ኃይል የስራ ስምሪትን የሚያበረታቱ መሆን እንደሚገባቸው መክሯል፡፡

የህግ የበላይነትን የሚያጎለብቱ የመልካም አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት፣ ሙስናን በተጠናከረ መልኩ መከላከልና በመንግስት፣ ሲቪል ማህበራት እና በህዝቡ መካከል ያለውን ቅንጅት ማጠናከር ተገቢ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ትብብር የተካሄደው ይህ ጥናት ተጠያቂነትና የአሰራር ግልጸኝነትን ማጠናከር ሁሉን አቀፍ ዕድገት በአገሪቱ በዘላቂነት ለማስፈን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አስቀምጧል፡፡

በተጨማሪም ጥናቱ የሁለተኛ ደረጃ፣ መደበኛ ያልሆነና የጎልማሶች ትምህርት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ አመልክቷል፡፡

የጥናቱ ሪፖርት በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ ፕሮግራም አስፈጻሚዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ውይይት አድርገውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም