በነቀምቴና ጅማ ከተሞች ኮሮናን በመከላከል በኩል የሚስተዋለው መዘናጋት አሳሰቢ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴና ጅማ ከተሞች ኮሮናን በመከላከል በኩል የሚስተዋለው መዘናጋት አሳሰቢ መሆኑ ተገለጸ
ነቀምቴ/ ጅማ፤ መጋቢት 25/2013(ኢዜአ) በነቀምቴና ጅማ ከተሞች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው አሰገዳጅ መመሪያ የመተግበር ጅምሮች ቢኖርም አሁን በአብዛኛው ላይ እየተስተዋለ ያለው መዘናጋት አሳሳቢ መሆኑን ተገለጸ።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ አመያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የወጡ ክልከላዎች ተግባራዊ እየተደረጉ አይደለም፡፡
በተለይም በትራንስፖርት አገልግሎት፣ ገበያ ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ቀብር ቦታዎችና በሌሎችም ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው ስፍራዎች የወጣው አሰገዳጅ መመሪያ በመተላለፍ የሚስተዋለው መዘናጋት አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ኮሮናን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ኃይሉን በማጠናከር ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን መመሪያውን የሚተላለፉ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደዱ አስታውቀዋል፡፡
የነቀምቴ ከተማ አስተዳር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው ሁሉም የፖሊስ አባላት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲጠቀሙ መደረጉንና በየሥራ ክፍሉ ’’ያለ ጭንብል አገልግሎት የለም’’ የሚሉ ጽሁፎች መለጠፋቸውን አስረድተዋል፡፡
በከተማዋ የጭንብል አጠቃቀምና ንጽህና መጠበቅ መቅረቱ እንዲሁም ርቀት አለመጠበቅ ጭምር የተፈጠረው መዘናጋት የግብረ ኃይሉ መዳከም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነቀምቴ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ፊጣ ሂካ በሰጡት አስተያየት ከመጋቢት 20/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሁሉም የባንኩ ሠራተኞች የአፍና አፍንጫ ጭምብል እየተጠቀሙ ነው ብለዋል።
ደንበኞች ያለ ጭንብል አገልግሎት እንዳያገኙ መደረጉንና የንጽህና መጠበቂያ መገልገያዎችም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የከተማዋ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፈየራ ዱጋሣ እንዳሉት፤ ሁሉም የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞችና ተገልጋዮች ጭምብል እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው፡፡
የደሣለኝ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ነገራ መኮንን የሆቴሉ ተገልጋዮች መንግሥት ያስቀመጣቸውን ክልከላዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ አስፈላጊው ቁጥጥርና ክትትል መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የጅማ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ኢንድያ መሀመድ እንደገለጹት ፤በኮሮናን መከላከል ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ለትራፊክ ፖሊሶች፣ ለመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች፣ ለሀይማኖት አባቶች ስልጠና ተሰጥቷል።
“ማስክ የምንገዛበት ዋጋ ትንሽ ነው፣ የምናጣው ህይወት ግን መተኪያ የለውም” ያሉት ሀላፊዋ ህብረተሰቡ ከመዘናጋት ወጥቶ ባለው አማራጭ ኮሮናን ለመከላከል ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአደጋ ጊዜ ክወና ማዕከል የሪስክ ኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ሀላፊ ዶክተር አብዱሰመድ ሁሴን የሚታየው መዘናጋት የበሽታውን መስፋፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው ተናግረዋል፡፡
በጅማና በአካባቢው ከሚመረመሩት የህብረተሰብ ክፍሎች 24 በመቶ ያህሉ የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።
ህብረተሰቡ እራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራና አስገዳጅ መመሪያውን በሚተላለፉት ላይ ፖሊስ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የገለጹት ደግሞ የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ሃላፊ ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አውግቸው ናቸው።
በከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተፈራ በዳዳ በሰጡት አስተያየት ’’እኔ ማስክ በማድረግ አምናለው፣ ነገር ግን ሰዎች ማስክ ሲጠቀሙ አላይም’’ ብለዋል፡፡
የበሽታው ስርጭት በየጊዜው እየጨመረ መሆኑ እየተነገረ ስለሚገኝ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ወጣት ምስር አሰፋ በበኩሏ "ሰሞኑን የተወሰኑ ሰዎች ማስክ ሲያደርጉ እያየሁ ነው ፤ ነገር ግን አብዛኛው ሰው ያለማስክ ሲንቀሳቀሱ ይታያል ብላለች፡፡
ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ መጠንቀቁ ለሁሉም እንደሚበጅ ገልጻለች።