የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ጀመረ
አርባምንጭ ፤ መጋቢት 25/2013( ኢዜአ) የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ / ጋዴፓ / የምርጫ ቅስቀሳውን ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ በይፋ ጀመረ።
ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሀጌ አንበሴ እንዳሉት፤ ጋዴፓ በስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለመወዳደር በጋሞ ዞን በሁሉም ወረዳዎችና በአዲስ አበባ ሁለት የምርጫ ክልሎች ዕጩዎችን አቅርቧል።
ካቀረባቸው ዕጩዎች መካከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘጠኝ፤ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ 25 መሆናቸውን አመልክተዋል።
የጋሞ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ፣ ለሀገሩ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ምሰሶና ማገር ሆኖ የኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ህዝቡ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ተጠቃሚ ባለመሆኑ የህዝቡን ችግር በመሠረታዊነት ለመፍታት ጋዴፓ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
ፓርቲው የምርጫ ህግና ስነ-ምግባር ደንቦችን በአግባቡ ከማክበርም በተጨማሪ ችግሮች ቢያጋጥሙ በውይይት ለመፍታት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በፓርቲው የአርባ ምንጭ ምርጫ ክልል የፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪ አቶ መርዕድ ሽብሩ በበኩላቸው በህገ-መንግስቱ መሰረት የፓርላማ አባላት ተጠሪነታቸው ለወከላቸዉ ህዝብ ቢሆንም ከሀገራችን አንፃር ይህ እየተተገበረ አይደለም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሀገሪቱ ፓርላማ በምሳሌነት ከሚጠቀሱት መካከል የሆኑት ከአፍሪካ እንደ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ፓርላማ ሞጋች መሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
እውነተኛ የህዝብ ውክልናን በማረጋገጥ በተለይ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡