የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ሁለት ጨዋታ በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ ተወሰነበት - ኢዜአ አማርኛ
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ሁለት ጨዋታ በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ ተወሰነበት
አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2010 የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በቀጣይ በሜዳው የሚያደርገው ሁለት ጨዋታ በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ ተወሰነበት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስነ ምግባር ኮሚቴ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ 30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የተከሰቱ የስፖርታዊ ጨዋነት የጎደላቸውን ተግባራት መርምሮ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል። በመጨረሻው ሳምንት ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 8 ሰአት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስና ሃዋሳ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ይጠቀሳል። በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ማጠናቀቂያ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያ የለበሱ ደጋፊዎች የሃዋሳ ከተማውን አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ስም እየጠሩ በመሳደባቸውና ቁሳቁሶችን ይወረውሩ እንደነበር የጨዋታው ኮሚሽነር ሪፖርት ማድረጋቸውን የስነ ምግባር ኮሚቴው ገልጿል። በጨዋታው 69ኛ ደቂቃ ላይ በቀኝ ጥላ ፎቅ የነበሩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የፌደራል ፖሊስ አባል ኮማንደር ጸጋዬ ተክሉ ከደጋፊዎች በተወረወረና ምንነቱ ባልታወቀ ቁሳቁስ ተመትተው እንደቆሰሉም ተገልጿል። 89ኛው ደቂቃ ላይ ደጋፊዎቹ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራን ስም በመጥራት አጸያፊ ስድብ ሲሰድቧቸው እንደነበረና የመቀመጫ ወንበርና ሳንቲም ወደ ፕሬዚዳንቱ እንደተወረወረባቸውና ፕሬዚዳንቱ ከችግሩ ለማምለጥ በፖሊስ ታጅበው መውጣታቸው ተጠቅሷል። ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የተጋጣሚውን ሃዋሳ ከተማ ክለብ አሰልጣኝ፣አመራሮችና ተጫዋቾችን ለመደብደብ መጋበዛቸውን ገልጾ ያም ቢሆን በጸጥታ አካላት አማካኝነት ችግሩ እንዲገታ መደረጉን የኮሚሽነሩ ሪፖርት እንደሚያሳይ ኮሚቴው ገልጿል። ችግሩ ሲፈጠር የክለቡ አመራሮች በስታዲየም ውስጥ የነበሩ ቢሆንም ችግሩ እንዲፈታ ምንም አይነት እርምጃ እንዳልወሰዱ ተጠቅሷል። ደጋፊዎቹ በፈጸሙት ተግባር የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በቀጣይ ከሜዳው የሚያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ያለ ተመልካች በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ መወሰኑን የስነ ምግባር ኮሚቴው አስታውቋል። ክለቡ የ150 ሺህ ብር ቅጣት አንዲከፍል የተወሰነ ሲሆን በጨዋታው ኮሚሽነር ሪፖርት መሰረት በስታዲየሙ ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ክለቡ የተጎዳውን ንብረት እንዲተካና አሊያም በገንዘብ እንዲከፍል መወሰኑን ኮሚቴው ገልጿል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተዘመገቡ ደጋፊዎቹን ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት በማስተማር ለፌዴሬሽኑ ማሳወቅ እንዳለበትና ይህን ካላደረገ ከፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ምንም አይነት አገልግሎት እንደማያገኝ ተገልጿል። ክለቡ በ10 ቀናት ውስጥ ቅጣቱን የማይከፈል ከሆነ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው ማንኛውም ውድድሮች እንደማይሳተፍ ኮሚቴው የገለጸ ሲሆን በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ የተወሰነውን ውሳኔ የሊግ ኮሚቴ እንዲያስፈጽም መወሰኑን አስታውቋል። በሌላ በኩል ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በጅማ ስታዲየም የሊጉ አሸናፊ ጅማ አባጅፋር ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲደረግ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስና የሃዋሳ ጨዋታ በተቋረጠባቸው አጋጣሚዎች ወደ ሜዳ ዘሎ በመግባት በተደጋጋሚ ጨዋታ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን የስነ ምግባር ኮሚቴ ገልጿል። በዚሁ መሰረት ደጋፊዎቹ በፈጸሙት ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር ጅማ አባጅፋር 150 ሺህ ብር እንዲቀጣ የተወሰነ ሲሆን ቀጣይ የሚያደርገውን ጨዋታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚመድበው ሜዳ ከሜዳው ውጪ እንዲጫወት እንዲደረግ ተወስኗል። ጅማ አባጅፋር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተመዘገቡ ደጋፊዎቹን ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት በማስተማር ለፌዴሬሽኑ ማሳወቅ እንዳለበትና ይህን ካላደረገ ከፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ምንም አይነት አገልግሎት እንደማያገኝ ተገልጿል። ክለቡ በ10 ቀናት ውስጥ ቅጣቱን የማይከፈል ከሆነ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው ማንኛውም ውድድሮች እንደማይሳተፍ ኮሚቴው የገለጸ ሲሆን ከሜዳው ውጪ ስለሚያደርገው ጨዋታ ውሳኔ የሊግ ኮሚቴ የሚያስፈጽመው እንደሆነ ተመልክቷል። ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም አርባምንጭ ከተማ ከፋሲል ከተማ ጋር ባደረጉት የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ በ68ኛው ደቂቃ አንድ የአርባ ምንጭ ከተማ ደጋፊ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ ተግባር በመፈጸሙ ጨዋታው ለ3 ደቂቃ መቋረጡንና የጸጥታ አካላት ችግሩን ጣልቃ በመግባት መቆጣጠራቸውን የኮሚሽነሩ ሪፖርት ላይ መገለጹን የስነ ምግባር ኮሚቴው ጠቅሷል። በዚሁ መሰረት ክለቡ ዳግመኛ ተመሳሳይ ቅጣት እንዳይፈጽም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰው ተወስኗል። ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም በ30ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናና መቀሌ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ ተግባራት መፈጸማቸው በጨዋታው ኮሚሽነር ሪፖርት ውስጥ መቅረቡ ተገልጿል። በዚሁ መሰረት ሁለቱ ክለቦች በፈጸሙት ተግባር ዳግመኛ ተመሳሳይ ቅጣት እንዳይፈጽም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው መወሰኑን ኮሚቴው አስታውቋል። በተጨማሪም ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በ28ኛ ሳምንት መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ማጠናቀቂያ አካባቢ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር ሲፈጽሙ እንደነበረና በጨዋታው ላይ የድሬዳዋ ከተማ አምስት ተጫዋቾች ቢጫ ካርድ መመልከታቸው የጨዋታ ሪፖርት መጠቀሱ ተጠቁሟል። በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ቡና ዳግመኛ ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይፈጽም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰውና የድሬዳዋ ከተማ ክለብ አምስት ተጫዋቾች ቢጫ ካርድ በማየታቸው ምክንያት ክለቡ 5 ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኗል። ሁሉም የቅጣት ውሳኔዎች የተወሰኑት የፌዴሬሽኑን የስነ ምግባር መመሪያ መሰረት አድርጎ መሆኑን የስነ ምግባር ኮሚቴው አስታውቋል። የስነ ምግባር ውሳኔዎች የሚወስናቸው ውሳኔዎች የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሙሉ ለመሉ የመሻር ወይም ቅጣቱን ሲቀንስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት የተስተዋለ ሲሆን ይህ በመሆኑ ምክንያት ክለቦች፣ዳኞችና የስፖርት ቤተሰቦች በተደጋጋሚ ጊዜ ቅሬታ ሲያቀርቡ