" ፀደይ " ባንክ ለክልሉ ልማት መፋጠን የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
" ፀደይ " ባንክ ለክልሉ ልማት መፋጠን የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገለጸ
ባህርዳር፤ መጋቢት 25/2013(ኢዜአ) የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም /አብቁተ/ መጠሪያውን ወደ "ፀደይ " ባንክ በማሸጋገር ለክልሉ ልማት መፋጠን የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገለጸ።
ተቋሙ ስምንት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ካፒታል ወደ ፀደይ ባንክ በመሸጋገር የመመስረቻ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በባህርዳር አካሂዷል።
በምስረታው ጉባኤ የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ ሊቀመንበርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት፤ አብቁተ ወደ ባንክ እንዲሸጋገር የታታሪ ሰራተኞች ድርሻ ከፍተኛ ነው።
ከብዙ ውጣውረዶች በኋላ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያለፈበት መንገድና ውጤታማነት ሲታይ ለቀጣይ ጉዞ ትምህርትና ልምድ ሊወሰድበት የሚገባ ነው ብለዋል።
ከአብቁተ የሚገኘው ትልቅ ትምህርት የችግር መፍትሄ ከሌላ ከመጠበቅ ይልቅ ከራስ የመፈለግ እሳቤ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚደርግ ሁሉም ሊማርበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የይቻላል መንፈስን ተላብሶ ጠንክሮ በመስራቱ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ካሉ ትልልቅ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ በሚሆንበት ደረጃ ላይ መድረስ የቻለ የፋይናንስ ተቋም መሆኑን አስታውቀዋል።
ተቋሙ ወደ ባንክ ሊሸጋገር የቻለው የክልሉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ፣ መዋዕለ ነዋያቸውን በልማት ላይ ለሚያፈሱ ባለሃብቶች ብድር ለማቅረብና ተወዳዳሪነቱን በተሻለ ደረጃ ለማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃና በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ባንክ ሆኖ በመውጣት ዋነኛ የልማት ሃይል እንዲሆን ለማስቻል ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አብቁተ የመተባበራችን፣ የአንድነታችንና የስኬታማነታችን ምልክት ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው።
ለወጣቶች፣ ባለሃብቶችና ለክልሉ ህዝብ ትልቅ አጋር የሆነው አብቁተ ከማይክሮ ፋይናንስ ወደ ባንክ መሸጋገሩ ወቅቱ የሚጠይቀውን የተቀላጠፈ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ያስችለዋል ብለዋል።
ክልሉ ለልማት ምቹ የሆነ መሬት፣ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ የከርሰ ምድር የውሃ ሃብት ባለቤት ቢሆንም ያሉትን ፀጋዎች በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ለተደጋጋሚ ችግር ሲዳረግ መቆየቱን አውስተዋል።
ዛሬ የተመሰረተው ፀደይ ባንክ ከክልሉ አልፎ በመላው ኢትዮጵያ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥና ያሉትን ፀጋዎች በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል::
የአንድነታችን ምሳሌና ማሳያ የሆነው ባንኩ ጠንክሮ እንዲወጣና ፈጥኖ ወደተሟላ እንቅስቃሴ እንዲገባም ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለተቋሙ እዚህ መድረስ የታታሪ ሰራተኞች፣ የተገልጋይ ደንበኞች፣ በየደረጃው ያሉ የተቋሙና የክልሉ አመራሮች ለውጤታማነቱ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወታቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውምወሰን በበኩላቸው የፋይናንስ ተቋሙ ሲመሰረት በክልሉ ውስጥ ስር የሰደደ ድህነትን ለመዋጋትና ብልፅግናን ዕውን ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ድህነት እንዲወገድና ህብረተሰቡ የተሻለ ኑሮ እንዲመራ የባንኩ መመስረት የጎላ ድርሻው እንዳለውም ገልጸዋል።
8 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ የተከፈለ ካፒታል የተመሰረተው ጸደይ ባንክ ከ793 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት አመልክተዋል።
በ1988 ዓ.ም. የተመሰረተው አብቁተ አሁን ላይ 1ሺህ 578 ቅርንጫፎች፣ የሳተላይት ጽህፈት ቤቶችና ከ12 ሺህ 600 በላይ ሰራተኞችን እንዳሉትም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ የቁጠባና ተበዳሪ ደንበኞች ያሉት ሲሆን ጠቅላላ ሀብቱም 36 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።