ቀጥታ፡

ምርጫው በህግ አግባብ እንዲከናወን የመታዘብ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ሲቪክ ማህበራት ገለጹ

ባህር ዳር ፤መጋቢት 25 /2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በመተማመን ላይ ተመስርቶ በህግ አግባብ እንዲከናወን የመታዘብ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በአማራ ክልል የሚገኙ ሲቪክ ማህበራት ገለጹ።

የክልሉ መምህራን ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ ሞላ ደሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ የሚካሄደው ምርጫ የሁሉንም አመኔታ ያተረፈ እንዲሆን በጠንካራ ትብብር መስራት ይገባል።

በተለይም ባለፉት ምርጫዎች የታዩ ስህተቶች እንዳይደገሙ የታዛቢዎች ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርጫው ዜጎች ላመኑበት ፓርቲ የሰጡት ድምፅ እንዲከበር ከአድልዎ በፀዳ አግባብ የመታዘብ ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በምርጫው በተንቀሳቃሽ ታዛቢነት የሚሳተፉ 73 የማህበሩ አመራሮች በስም ዝርዝር ከነአድራሻቸው በማዘጋጀት ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውንም ጠቅሰዋል።

በሚታዘቡበት ወቅት የሚታዩ ግድፈቶችን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ለወከላቸው ወይም በአቅራቢያ ለሚገኝ አካል ፈጥኖ በማቅረብ ችግሩ እንዲፈታ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

መራጩ ህዝብም ከአላስፈላጊ ስሜት ወጥቶ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ዕድገት ሊያሻግር የሚችልና ህዝቡን ለማገልገል ዝግጁ የሆነ ትክክለኛ ማኒፌስቶ ያላቸውን ፓርቲዎች ለይቶ መምረጥ ይኖርበታል ብለዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚመርጠውን ህዝብ ድምፅ የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በተለይ ወጣቱ በምርጫ ወቅትና በኋላ ወደ ግጭት ሊያስገቡ ከሚችሉ ነገሮች ራሱን አርቆ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

'ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን  የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ መኮንን ታከለ ናቸው።

በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ከሚገኙ 198 መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበራት መካከል እስከ 24 በመቶ የሚሆኑትን በምርጫው በታዛቢነት እንዲሳተፉ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ታዛቢዎችም ምርጫው ከመድረሱ በፊት ተገቢውን ስልጠና በምርጫ ቦርድ እንዲወስዱ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

በምርጫ ወቅት ያልተገባ ነገር ሲያዩ ፈጥነው ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ችግሩ ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ  ከማምራቱ በፊት መፍትሄ እንዲያገኝ  እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ግጭት እንዲነሳ ለሚያደርጉ አካላት ተባባሪ ባለመሆን ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ሊዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

መንግስትም በምርጫ ወቅት ምርጫውን የሚያደናቅፉ ነገሮች እንዳይፈጠሩ አስፈላጊው የፀጥታ ኃይል ከወዲሁ ማዘጋጀት እንዳለበትም አቶ መኮንን አመልክተዋል።

ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በመጪው ግንቦት ወር  እንደሚካሄድ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም