ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ የግብርና ተፋሰስ ልማት ዘርፎች ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል- ጠቅላይ ሚኒስትሩ - ኢዜአ አማርኛ
ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ የግብርና ተፋሰስ ልማት ዘርፎች ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል- ጠቅላይ ሚኒስትሩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረጓ በግብርና እና ተፋሰስ ልማት ዘርፎች ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሳምንት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ እውን መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚሁ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ደመናን ወደ ዝናብ በመቀየር ረገድ በጎጃም እና ሸዋ አካባቢዎች የተሳካ ሙከራ መደረጉንም ይፋ አድርገዋል።
ይህን ተከትሎም ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በእንጦጦ ኦቭዘርቫቶሪ ምርምር ማእከል ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ስራ ተከናውኗል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድ፤ በዚሁ ወቅት ዓለማችን በከፍተኛ የቴክኖሎጂ አብዮት ውስጥ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በበርካታ የዓለማችን አገሮች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ናኖ ቴክኖሎጂ ስራ ላይ መዋሉንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአንጻሩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ለልማት በማዋል ረገድ ብዙ እንደሚቀራትም አንስተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም ከዓመት በፊት ኢትዮጵያ ወደ ህዋ ሳተላይት ማምጠቋን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ መቀየር መጀመሯም የዚሁ ትኩረት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ለበርካታ ዓመታት ደመና በላያችን ላይ እያለፈ ሌሎች ሀገራት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል ያሉት ዶክተር አህመዲን፤ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በቂ ዝናብ ማግኘት ጊዜ የሚሰጠው ተግባር እንዳልሆነ አብራርተዋል።
ዝናብ ካለ ውሃ አለ፤ ውሃን ደግሞ ቁጭ ብሎ በመጠበቅ ብቻ ማግኘት አይቻልም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ስኬት ማስመዝገቡን አስታውሰዋል።
ቴክኖሎጂው በተለይ በርካታ ሃብት አውጥተው የሃይልና መስኖ ግድብ ለሚገነቡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ተፋሰሶች በቂ ውሃ እንዲያገኙ በማድረግ ለመስኖ ልማትና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች እንጠቀመዋለን ብለዋል።
ነገር ግን መንግስት ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ተጠቅማ ጸጋዎቿን እንድታለማ የያዘው ውጥን እውን የሚሆነው ዜጎች ለሰላምና ወንድማማችነት ቁርጠኛ ሲሆኑ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በለመደችው የድህነትና መከፋፋል አዙሪት እንድትቀጥል የሚፈልጉ ሃይሎች ተላላኪ ሽፍቶችን በመቅጠር ንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ሃይሎች ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ቀን ከሌት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም ሁላችንም የአንድ ዜጋ ሞት የኢትዮጵያ ሞት እንደሆነ ተገንዝበን ያለምንም መከፋፋል በጋራ መቆም አለብን ነው ያሉት።
በሀገር ውስጥ ትርምስ ለመፍጠር የሚሰሩ ተላላኪ ሽፍቶችን የምናጠፋበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተላላኪ ሽፍቶች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
"አፋቸውን የከፈቱ ጅቦች ትንንሽ አይጦችን በመላክ ኢትዮጵያን ለመዋጥ ለሚያደርጉት ሙከራ እድል መስጠት አይገባም" ሲሉም ገልጸዋል።
እነዚህ እኩይ ሃይሎች በቀደዱት ቦይ ከመፍሰስ ተቆጥበንና አንድነታችንን አጠናክረን ህልማቸውን ማክሸፍ አለብን ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአውሮፕላን፣ በድሮን ወይም ከፍ ባሉ ቦታዎች ላይ በሚቀመጡ ጀኔተሮች አማካኝነት ወደ ደመና ኬሚካል በመርጨት ዝናብ እንዲዘንብ ይደረጋል።
በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ኬሚካልን ወደ ደመና የሚረጭ ጀነኔተር የተተከለ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ቴክኖሎጂውን ጎብኝተውታል።
በተጨማሪም አውሮፕላንን በመጠቀም ደመናን የማዝነብ ተክኖሎጂ ምን እንደሚመስል ትውውቅ ተደርጓል።
ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ በዓለም ከ56 አገራት በላይ ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።