የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለማጠናከር መዘጋጀቱን የግል ከፍተኛ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማህበር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለማጠናከር መዘጋጀቱን የግል ከፍተኛ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማህበር አስታወቀ
አዲስ አበባ መጋቢት 25 ቀን 2013/ ኢዜአ/ ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በመተግበር በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት መስራት መጀመሩን የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማህበር አስታወቀ።
ማህበሩ 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምክክር አካሂዷል።
ጉባኤውን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላ ጸጋዬ እንደገለጹት በአገሪቱ ከመንግስትም ሆነ ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በርካታ ምርምሮች ይደረጋሉ።
ይሁን እንጂ ምርምሮቹ ከቁጥጥር የዘለለ እምብዛም ተጨባጭ ውጤት አላመጡም ብለዋል።
በመሆኑም ተቋማቱ በቀጣይ ችግር ፈቺና ተጨባጭ የምርምር ውጤቶች ላይ በማተኮር ለውጥ ማምጣት ይሰራሉ ብለዋል።
በተለይም የግሉ ዘርፍ ከትምህርት ጥራት ጋር ያሉበትን ክፍተቶች በመለየትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንዲሰሩ በማድረግ ማህበሩ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ሂደት የግብአት አቅርቦት፣ የመስሪያ ቦታና የባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ከመንግስት የሚጠበቅ ድጋፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ የትምህርት ተቋማቱ ምቹ አለመሆንና በቂ ግብአት አለመሟላት አይነተኛ ችገሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የትምህርት ማእከላት ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ምቹና አስተማማኝ ሆነው እንዲገነቡ ለማስቻልም ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ተቋማቱ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ፈጠራዎች ላይ በማተኮር የአገሪቱን አሁናዊ ሁኔታ በማገናዘብ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በዘርፉ አዳዲስ ፕሮግራሞች ሲቀረጹ የአገሪቱን ፍላጎትና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ማገናዘቡንም መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ በሙያ ከማብቃት ባሻገር በማእድን ዘርፎች ላይም እንዲሁ ብርቱና ስኬታማ ዜጋን ማፍራት ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ወቅቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራርን የሚጠይቅ በመሆኑ ትውልዱን ለማዘመንና ህብረተሰቡ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ዘርፉ ጥራት፣ ፍትሃዊነት፣ አግባብነትና ተደራሽነት የተላበሰ እንዲሆን መሰናሰል ያስፈልጋል ለዚህም ተቋማቱ ከመንግስት ተቋማት ጋር ያላቸውን ትብብር ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ማህበር አሁን ላይ 131 አባላት እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ።