ዩኒቨርሲቲዎች የሳይንስ፣ ምህንድስና እና የሂሳብ ማዕከላትን እንዲያቋቋሙ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎች የሳይንስ፣ ምህንድስና እና የሂሳብ ማዕከላትን እንዲያቋቋሙ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ መጋቢት 25/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች የሳይንስ፣ምህድስናና ሂሳብ ማዕከላትን እንዲያቋቋሙ የሚያግዝ መመርያ መዘጋጀቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ስቴምፓወር ከተሰኘው ድርጅት ጋር በመተባበር ሂሳብ፣ ቴክኖሎጂና ምህንድስና በአገሪቷ ሊጠናክር በሚችልበት ጉዳዮች ላይ አውደ ጥናት አካሂዷል።
አውደ ጥናቱ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስ ባህል ግንባታ ዳይሬክተር ዶክተር ዱላ ቶሌራ እንደተናገሩት፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት ያለው ትውልድ ማፍራት ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው።
በተለይም ሂሳብ፣ ምህድስናና ቴክኖሎጂዎች ላይ የተለየ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች መደገፍ ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች በሳይንስ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ ያላቸውን እውቀት በላብራቶሪ ታግዘው ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱንም ነው የጠቆሙት።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ ባህዳር፣ ሀዋሳ እና አዳማ ዩኒቨርስቲዎች ማዕከላቱን አቋቁመዋል።
ሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም ባላቸው አቅም ልማት አሟልተው ወደ ሥራ እንዲገቡ በመመሪያው መሰረት ለተቋማቱ ድጋፍ እንደሚደረግም አብራርተዋል።
መመሪያው በተለይም ሁሉም ዩኒቨርሰቲዎች ዘርፉ ላይ የሚሰሩት ስራ ውጤታማ እንዲሆን ወጥ የሆነ አሰራር እንዲዘረጉ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ዩኒቨርስቲዎች ምን መስራት አለባቸው? የሚለውን ዝርዝር ነገሮች ተለይተው የተቀመጡበት እንደሆነም አክለዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብልጽግና ተምሳሌት አገር ለመሆን ራዕይ መሰነቋን ጠቁመው ለዚህ ደግሞ የሰለጠነ የሰው ሃይል ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማውጣት ደግሞ በሳይንስ፣ ምህድስና እና ሂሳብ ዘርፎች ላይ መስራት ለትምህርት ጥራት አወንታዊ ሚና ያለው መሆኑን ነው ያብራሩት።
የስቴም ፓወር ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ወይዘሪት ቅድስት ገበረአምላክ፤ ድርጅቱ በዘርፉ ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች ባሉት ማዕከላት እየደገፈ መሆኑን አመልክተዋል።
አሁን ድርጅቱ 48 ማዕከላት ያቋቋመ ሲሆን በማዕከላቱ ቤተ ሙከራዎች ተማሪዎች በተለያዩ የሳይንስ መስኮች እውቀታቸውን የሚያዳብሩበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል።
የተለያዩ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ዜጎችም ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ሁኔታ መመቻቸቱም ያስታወሱት ዳይሬክተሯ ይህም የሳይንስ ባህል እንዲጎለበት የሚያደርግ ነው ብለዋል።