ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አልማዝዬ ሜዳ በመገኘት ለቄራ አንበሳ ስፖርት ማኅበር ትጥቅ አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አልማዝዬ ሜዳ በመገኘት ለቄራ አንበሳ ስፖርት ማኅበር ትጥቅ አበረከቱ
አዲስ አበባ መጋቢት 25/2013/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ቄራ አካባቢ በሚገኘው አልማዝዬ ሜዳ በመገኘት ለቄራ አንበሳ ስፖርት ማህበር የትጥቅ ድጋፍ አደረጉ።
ምክትል ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት “ስፖርትን መደገፍ አጠቃላይ አብሮነትንና ወንድማማችነትን መፍጠር” በመሆኑ ድጋፍና እገዛው ይቀጥላል።
አልማዝዬ ሜዳ በርካታ ስፖርተኞችን ያፈራ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ በዚህም በዘመናዊ መልኩ የሚገነባ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በቀጣይ ሜዳውን ሣር የማልበስ ፣ መታጠቢያና መፀዳጃ ቤቶችን መሥራት፣ የስፖርት ትጥቆች መሸጫ ሱቆችን የመገንባት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
ስፖርተኞች ከውድድር ባለፈ ለሀገር ልማትና ሰላም ግንባታም ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ከንቲባዋ ለአብንሮነትና ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው በስፖርቱ ዘርፍ የማዘውተሪያ ሥፍራ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልፀው ከተማ መስተዳድሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
እውቁ ባለሀብት አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው ስፖርት ለሰዎች አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው ለአልማዝዬ ሜዳ ግንባታ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፤ ፌደሬሽኑ ከባለሀብቶች ጋር በመተባባር የሙያና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።