ቀጥታ፡

በኡጋንዳ የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድር ብሔራዊ ቡድኖቻችን ድል ቀናቸው

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 በኡጋንዳ እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አሸነፉ። ዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያካሄደው ውድድር ትናንት በይፋ ተጀምሯል። ኢትዮጵያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች በሁለት ብሔራዊ ቡድኖች የተወከለች ሲሆን ሁሉም ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ድል አድርገዋል። በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ግርማ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የጅቡቲ አቻውን 10 ለዜሮ በሆነ ሰፊ ልዩነት ረትቷል። በአሰልጣኝ መሐመድ አህመድ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የኬንያ አቻውን 33 ለ 21 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በቀጣይ ቀናት ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል። በኡጋንዳ ርዕሰ መዲና ካምፓላ የሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድር እስከ ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል። የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ውድድር ላይ አዘጋጇ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ጂቡቲ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በ2006 እና በ2007 ዓ.ም የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ውድድርን ማስተናገዷ የሚታወስ ሲሆን ሁለቱም ውድድሮች በአሸናፊነት አጠናቃለች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም