ቀጥታ፡

ኮሪያ ለኢትዮጵያ በረዥም ጊዜ ብድር የሚከፈል የ30 ሚሊዮን ዶላር የህክምና መሳሪያዎችን ሰጠች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24/2013 ( ኢዜአ) ኮሪያ ለኢትዮጵያ በረዥም ጊዜ ብድር የሚከፈል የ30 ሚሊዮን ዶላር የህክምና መሳሪያዎችን ሰጠች።

የህክምና መሳሪያዎቹን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በኢትዮጵያ ከኮሪያ አምባሳደር ሚስተር ካንግ ሶኪ በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ርክክብ አድርገዋል።

በዚህም  ከ30 በላይ የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች የተካተቱ ሲሆን በተለይ ለኮቪድ-19 ጽኑ ህሙማን ታካሚዎች የሚረዱ የመተንፈሻ ቬንትሌተሮችን ጨምሮ፣ የፅኑ ህሙማን መተኛ አልጋዎች፣ የኮቪድ መመርመሪያ ኪቶችና ሌሎችም ይገኙበታል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኮሪያ መንግስት መካከል የተደረገው የህክምና መሳሪያዎች ግዥ የብድር ስምምነት በረዥም አመታት የሚከፈልና ወለዱም በጣም ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ መሆኑን ገልጸዋል።  

በተለይ ለኮቪድ 19 ጽኑ ህሙማን የሚረዳና የጽኑ ህክምናን ለማስፋፋት የሚያግዝ ነው ያሉት ሚኒስትሯ አሁን የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ መጠነ ሰፊ የሆነ ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉትን የህክምና ማዕከላት አቅም ለማስፋፋትና ለመገንባት ትልቅ እስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የኮሪያ መንግስት ለኢትዮጵያ ላደረገው ትብብርና ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ሚስተር ካንግ ሶኪ በበኩላቸው፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ  አንስቶ መንግስታቸው ለኢትዮጵያ በርካታ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን ገልጸዋል።

በዛሬው እለትም በኮሪያ በኩል የተደረገው የ30 ሚሊዮን የረዥም ጊዜ ብድር ሶሰት ዋና ዋና ጉዳዩችን መሰረት አድርጎ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም ወዳጅነትን ለማጠናከር፣ የማህበረሰብ ጤናን ለማሳደግና ወረርሽኙን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።

''የኮሪያ እና የኢትዮጵያ ወዳጅነት 70 አመታትን የተሻገረና ጠንካራ ትብብር ያለው መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም