ቀጥታ፡

የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ ለብሔራዊ መግባባት ጉልህ አስተዋጽኦ ስላለው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመለከተ

አርባ ምነጭ ፤ መጋቢት 24/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ ለብሔራዊ መግባባት ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመለከተ።

አገር አቀፍ የትርጉም ጉባዔ ዛሬ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋ፣ የስነ-ቃልና ትርጉም ልማት ዳይሬክተር ዶክተር አውላቸው ሹምነካ በወቅቱ እንዳሉት ፤ ሀገሪቱ  ከ80 በላይ የብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋዎች ባለቤት ብትሆንም ለትርጉም ሙያ ትኩረት ባለመሰጠቱ በመስኩ ተጠቃሚ አልሆነችም።

በተለይ ትርጉምና አስተርጓሚ ሙያ ለብሔራዊ መግባባት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉ በዕውቀት እንዲመራ ለማድረግ ሚኒስቴሩ  ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር  እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጉባዔውም ስለትርጉምና አስተርጓሚ ሙያ ግንዛቤ ለመፍጠርና ለስርዓተ ትምህርት ፖሊሲ ግብአት ለማሰባሰብ   መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ጥራት ያለው የትርጉም ስራ ካልተገነባ ሀገር  ሊጎዳ እንደሚችል የተናገሩት  ዶክተር አውላቸው በዚህ ረገድ ትኩረት በመስጠት ጥንቃቄና ኃላፊነት ተወስዶ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባህልና ቋንቋ ትምህርት ክፍል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰይድ አህመድ በበኩላቸው ትርጉምና አስተርጓሚነት በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ያለው ቢሆንም እንደ አንድ ሙያ ሳይታይ መቆየቱን አውስተዋል።

በሀገሪቱ  ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የምልክት ቋንቋ ተጠቃሚ ዜጎች መኖራቸውን ጠቅሰው  እነዚህ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የትርጉምና አስተርጓሚ ሙያ ማደግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ይህም ህዝቦች በፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች የሚኖራቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሊያሳድግ የሚችል በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልከተዋል።

የምልክት ቋንቋና አስተርጓሚነት በኢትዮጵያ ደረጃ እንደ ሙያ ሳይሆን እንደ ረጂ ተረጂ አካሄድ ሲታይ የቆየ ነው ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋና መስማት የተሳናቸው ባህል ጥናት መምህር ዶክተር ኢያሱ ሃይሉ ናቸው።

ከ50 ዓመት በፊት ጀምሮ የምልክት ቋንቋ አገልግሎት በፍርድ ቤት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ጤናና ሃይማኖት ተቋማት እየተሰጠ ቢመጣም  በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ አለመኖሩን ገልጸዋል።

በሀገራችን 53 ቋንቋዎች  ለመማሪያና ምርምር እያገለገሉ መሆናቸውን ጠቅሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ጉባዔው ለችግሮች መፍትሄ  ሊጠቁም እንደሚችል ተናግረዋል።

የትርጉም ሙያን ለማዘመን ዘርፉ በስልጠና፣ ጥናትና ምርምር በመደገፍ በዘርፉ የበቃ  የሰው ሃይል መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴርና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት  ባዘጋጀው ጉባዔ   የዘርፉ ምሁራንና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን ከትርጉም ስራ ጋር የተያያዙ   ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው  ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም