ሀገራዊ ሪፎርሙ እና ተስፋዎቹ

15

ሀገራዊ ሪፎርሙ እና ተስፋዎቹ

በአብዱራህማን ናስር (ኢዜአ)

የዛሬ ሶስት ዓመት በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም የመጀመሪያው ሳምንት የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው “በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የተከሰተውን አለመረጋጋትና የፖለቲካ ችግር በዚህም ምክንያት በርካታ የሰው ህይወት መጥፋት፣ ከአካባቢያቸው የመፈናቀል እንደዚሁም ደግሞ የንብረቶች መውደም ኢንቨስትመንቶችን የማስተጓጎል እና ኢንቨስተሮች እንዲወጡ በማድረግ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችላቸው በአህአዴግ ደረጃም በመንግስት ደረጃም የተለያዩ ሪፎርሞችን በመጀመር እነዚህን ሪፎርሞች ለማሳካት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እኔም በበኩሌ ለእነዚህ ሪፎርሞች መሳካትም ሆነ ላስቀመጥናቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች የመፍትሔው አካል ለመሆን በማሰብ በገዛ ፍላጎቴና ፈቃዴ የኢህአዴግ ሃላፊነትንም ሆነ የመንግስት ሃላፊነቴን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርቤአለሁ፤” በማለት ያደረጉት አጭር ንግግር በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንፃር ቀጣዩ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ በብዙዎች ዘንድ ፍርሃትና ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር።

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ሀገሪቱን ሲያስተዳድር በቆየባቸው ጊዜያት ተንሰራፍቶ በነበረው ብልሹ አሰራርና ሥር የሰደደ ሙስና እንዲሁም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሱ በመምጣታቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ህዝባዊ ተቃውሞ ገንፍሎ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ በመውጣቱ ነበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ የተገደዱት። በወቅቱ በየአቅጣጫው እየበረታ የመጣውን ህዝባዊ አመጽ ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገ ቢሆንም የጸጥታ ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ የሚሞቱ ሰዎች ከቀን ወደ ቀን እንዲያሻቅብ ማድረግ እንጂ ማርገብ አልተቻለም። በዚህ ምክንያት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ረጅም ቀናትን የወሰደ ግምገማ ካደረገ በኋላ በሰጠው መግለጫ የችግሮቹ መንስኤዎች የአመራር ድክመት መሆናቸውን አመልክቷል። ይህን ተከትሎ ፓርቲውን በሊቀ መንበርነት፣ ኢትዮጵያን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲያስተዳድሩ ዶ/ር ዐብይ አህመድን መሪ አድርጎ መርጧል።

ይህ የአመራር ለውጥ በተለይም የዶ/ር ዐብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጥ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ ወዳጆች ዘንድ ትልቅ ደስታን የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር ለሀገሪቱም እፎይታን ያመጣ ነበር። ይህ የለውጥ አመራር በሀገር ውስጥ እና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ የተሰጠው ሲሆን የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎችም “የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚያጠናክር፣ በሕዝቦች መካከል ትስስርን የሚፈጥር ነው” በማለት ነበር የገለጹት።

አዲሱ አመራር ስልጣን ከተረከበ ማግስት ጀምሮ በወሰዳቸው የሪፎርም እርምጃዎች አብዛኛዎቹ በህብረተሰቡ ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች ለመመለስ ያስቻሉ ናቸው። ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል በማረሚያ ቤቶች የነበሩ የፓለቲካ እስረኞች መፈታት፣ ወደ ውጭ ሀገር ተሰደው የነበሩ እንዲሁም የትጥቅ ትግል ያደርጉ የነበሩትንም ጭምር በነጻነት ወደ  ሀገራቸው  እንዲመለሱ  መደረጉ፣ መብትን ይገድባሉ በሚል አቤቱታ ይቀርብባቸው የነበሩ ህጎች እንዲሻሻሉ መደረጋቸው በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የዴሞክራሲ ተቋማት በአዲስ መልክ እንዲደራጁ፤ የፍትህ ተቋማት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱና በህዝብ ዘንድ ያላቸውን አመኔታ ለማሳደግ ገለልተኛ ሆነው እንዲቋቋሙ ለማድረግ መሰረታዊ ለውጥና ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል። በተመሳሳይ የፀጥታ አካላት ህግና ስርዓትን የማስከበር ተልዕኳቸው ከፖለቲካ ውግንና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ማከናወን እንዲችሉ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡

በኢኮኖሚው መስክ ሀገሪቱ አጋጥሟት የነበረውን የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት ለማስተካከል የግሉን ዘርፍ በዋናነት በኢኮኖሚ ውስጥ የማሳተፍ ዓላማ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተደርጓል። ይህንን አስመልክተው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በወቅቱ እንደገለጹት ቀደም ሲል የነበረው የኢኮኖሚው መዋቅር ለግሉ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደነበርና በርካታ ማነቆዎች እንደነበሩበት አመልክተው የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂ አድርጎ ለማስቀጠል፣ የወጣቶችን አቅም ለመጠቀምና የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማጎልበት ያለመ ሪፎርም መከናወኑን ጠቁመዋል።

ሌላው ሀገራዊ ሪፎርሙ ትኩረት ካደረገባቸው ዘርፎች መካከል የሀገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ በተለይ ከፍተኛ መጓተት የታየባቸውን በአዲስ መልክ በመከለስ በፍጥነት የሚጠናቀቁበት እርምጃ ተወስዷል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ሲሆን በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በኩል በተፈጠሩ ግድፈቶች ምክንያት ይጠናቀቃል ከተባለው ጊዜ በአራት ዓመት በመዘግየቱ የህዝቡ ሞራል እንዲያሽቆለቁልና በመንግስት ላይ የነበረው አመኔታም እንዲቀንስ አድርጎ ነበር። ስለሆነም በፕሮጀክቱ ዙሪያ የነበሩትን አጠቃላይ ችግሮች በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በተደረገው መሰረት ግንባታው አሁን ወደ 79 በመቶ ሊደርስ ችሏል። እርምጃውም በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳትና እምነት እንዲፈጠር አድርጓል። ይህ የህዝቡ መነሳሳት ከህዳሴው ግድብ ባሻገር እንደ ገበታ ለሀገር በመሳሰሉ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ገንዘቡን በማዋጣት በተገኘው ለውጥ ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጎታል።      

ሀገራዊ ለውጡ በዲፕሎማሲው መስክ ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል ትልቅ ድርሻ የሚወስደው ከኤርትራ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን በመጡ በአራተኛው ወር ሐምሌ 2010 ዓ.ም. ወደ ኤርትራ መጓዛቸው የዓለም መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ አጀንዳ ነበር። በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ በመቆየቱ እንዲሁም በፍጥነት ይሻሻላል የሚል ግምት ባለመኖሩ ሁኔታው ግርምት ፈጥሯል። ታዋቂው የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ “ከ20 ዓመታት ወታደራዊ ፍጥጫ በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማደስ ድንገተኛና አስደናቂ የሆነ ስምምነት አደረጉ” በማለት ነበር ሁነቱን የዘገበው። ከመገናኛ ብዙሃኑ ባሻገር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ትኩረት የሰጠው ክስተት ሲሆን የተዋለዱና በተፈጠረው ሁኔታ ተለያይተው የቆዩ በሁለቱ ሀገራት የሚገኙ ቤተሰቦችንም እንባ በማራጨት ያገናኘ ክስተት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ይህ የለውጥ ሂደት ባለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ አዎንታዊ እርምጃዎች የተወሰዱበትና በርካታ ስኬቶች የተገኙበት የመሆኑን ያህል ተግዳሮቶችም አልተለዩትም። በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ተስፋን የሚያጨልሙ ግጭቶች፣ የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም ተከስቷል፤ አሁንም እየተከሰተ ነው፡፡ እነዚህ ክስተቶች በአንድ በኩል ለረጅም ጊዜያት ህዝቡ ከመተማመን ይልቅ እርስ በርሱ እንዲጠራጠር በተሰራው ስራ በሌላ በኩል ደግሞ በለውጡ ቅቡልነት ደስተኛ ያልሆኑ አካላት በተቃራኒ በመቆም በተለያየ መልኩ ባደረጓቸው ቅስቀሳዎች የተፈጠሩ ናቸው።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በዓይነታቸው የተለያዩ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች እና ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች በስፋት ሲሰራጩ ነበር። በዚህም ምክንያት የዜጎች ህይወት ጠፍቷል፣ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፤ ንብረት ወድሟል። ሀገራዊ ለውጡ ስድስት ወራት እንኳ ሳያስቆጥር በአዲስ አበባ ዙሪያ በተለይ በቡራዩ ከተማ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር እንዲሁም በሶማሌ እና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች አስቀድሞ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የደረሰው መፈናቀል፣ ግድያና የንብረት ውድመት እንዲሁም በጉጂና ጌዴኦ ዞኖች አዋሳኝ ቀበሌዎች የተፈጠረው የዜጎች መፈናቀልና አለመረጋጋት ቀላል ተግዳሮት አልነበረም።

በተመሳሳይ በኦሮሚያና አማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ አዲስ አበባና ድሬደዋ የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፍ በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ ስጋት እንዲነግስ ያደረጉ ኹነቶች አጋጥመዋል። በዜጎች ላይ ከሚሰነዘረው ጥቃት በተጨማሪ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ግድያም ተፈጽሟል። ይህ በዜጎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት አሁንም ድረስ ዘልቆ በምእራብና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ እንዲሁም በደቡብ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት የጅምላ ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ይገኛል።

እነዚህንና መሰል ችግሮች መንግስት የህግ የበላይነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ስራ እየሰራ አይደለም በሚል ከፍተኛ ትችትን እያስከተሉ ይገኛሉ። እነዚህ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ካልተቀረፉ ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋ የጣለበትን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይቀለበስ ብዙዎች ስጋት አላቸው፡፡ አሁን ከየትኛውም ጊዜ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም ዴሞክራሲ ማበብ እድል የሚሰጥ የተሻለ እድል እየመጣ ስለመሆኑ የብዙዎች እምነት ነው፤ ነገር ግን የህግ የበላይነት ካልተረጋገጠና አጥፊዎች ተጠያቂ ካልተደረጉ ሀገራዊ ለውጡ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደማይችል ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል የህወሃት ጁንታ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል በተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ የተለያየ አጀንዳ ያላቸው የውጭ አካላት ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ከፍተኛ ዘመቻ ከፍተዋል። የህዳሴው ግድብ ስራ በስኬት እየተጠናቀቀ በመምጣቱና ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ በመሆኑ ግብጽ እና ሱዳን ከምን ጊዜውም በላይ በየእለቱ ዛቻና ማስፈራሪያ እያሰሙ ይገኛል። ግንቦት ወር የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝቡ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዳይጠናቀቅ ከውስጥም ከውጭም ያለእረፍት እየሰሩ ይገኛል።     

ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ወቅት በአንድ በኩል ሪፎርሙ ባመጣቸው ለውጦች ህዝቡ ትልቅ ተስፋ የሰነቀበት፤ በሌላ በኩል ለውጡ ወደፊት እንዳይሄድ ቢቻል አደናቅፎ ለማስቀረት ካልሆነም ለማስተጓጎል ትግል የሚደረግበት ነው። ስለሆንም የተጀመሩትን የለውጥ እርምጃዎች ወደፊት ለማስቀጠል ከምንም በላይ ውስጣዊ ሁኔታችን ወሳኝ ነውና ህዝቡ የአንድነት እሴቶቹ ላይ ማተኮር ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ማጠናከር እስከቻሉ ድረስ ወደፊት ከመሄድ የሚያቆማቸው እንደሌለ ትናንትናቸው ምስክር ነው።      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም