ቀጥታ፡

በለውጡ የሚገጥሙ ፈተናዎችን መፍታት ለተወሰነ አካል ብቻ የሚተው አለመሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ሂደት የሚገጥሙ ፈተናዎችን መፍታት ለተወሰነ አካል ብቻ የሚተው ጉዳይ ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ ድርሻ የሚጠይቅ መሆኑ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሀገር መሪነት የመጡበት ሶስተኛ ዓመት በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በፓናል ውይይት ተከብሯል።

በመድረኩም የፌደራልና ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

የፕራይም ሚዲያ መስራች ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ለውጡ ያስመዘገባቸው ስኬቶች፣ የገጠሙ ፈተናዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የያዘ የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ጫልቱ ሳኒ፤ በውይይቱ ላይ እንዳነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡባቸው ቀደም ብለው ባሉ ጥቂት ጊዜያት ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ነበረች።

ተፈጥሮ የነበረው ቀውስም የኢትዮጵያን ህልውና የተፈታተነና በመደበኛ የህግ ስርዓት ማስተካከል ያልተቻለ ነበር ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይቅርታንና ወንድማማችነትን ያነገበ ሪፎርም ይዘው በመምጣት ቀውሱን ለመፍታት መቻላቸውንም አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትናንትን ጨለማ በዛሬ ብርሃን መፍታት የሚያስችል አዲስ የአመራርነት ባህል ይዘው የመጡ ናቸውም ብለዋል።

ያለፉት ሶስት ዓመታት ጉዞ ሪፎርም እንጂ አብዮት ባለመሆኑ ሂደቱ አልጋ ባልጋ እንዳልነበርም ምክትል ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በወንድማማችነት መንፈስ በመተሳሰብ የገጠሙንን ፈተናዎች በአጭር ጊዜ መፍታት አለብንም ነው ያሉት።

የፕራይም ሚዲያ መስራች ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ በበኩላቸው ኢህአዴግ በትረ ስልጣኑን ከደርግ ከተቀበለ በኋላ የኢትዮጵያ ጥያቄ የብሔር ጥያቄ ብቻ ነው በሚል እሳቤ ልዩነትን በስፋት ማራገቡን ጠቁመዋል።

ቀደም ያሉ ቂምና ቁርሾዎችን በይቅርታ ከመፍታት ይልቅ በሃይል ለመደፍጠጥ መሞከሩም ሌላኛው ችግር መሆኑን  አስታውሰዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ወቅት ከተፈጠሩ ቁርሾች ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን ወደ ቀውስ እንድታመራ እንዳደረጋትም ገልጸዋል።

ችግሩ ቀስ በቀስ እየሰፋ ሄዶ ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነት ማምራቱን በመግለጽ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት በመጡ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ የነበረውን ቀውስ ከመቅረፍ ባለፈ ሌሎች ታላላቅ ስኬቶችን ማስመዝገባቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የህግ ማሻሻያዎች፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረውን እርቅ ለአብነት አንስተዋል።

በሂደቱ ብዙ ፈተናዎች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው፤ ፈተናዎቹን በማለፍ ለውጡ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ማስቀጠል የሚቻለው ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሲወጣ ነው ብለዋል።

ለውጡ ለተወሰነ አካል ብቻ መተው እንደሌለበት በማብራራት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለውጡ በፈተና ውስጥ ሆኖ የሚያስደንቁ ስኬቶችን ማስመዝገቡን እያንዳንዱ ዜጋ ሊገነዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመሆኑም ለውጡ ይዞት የመጣውን እድልና ተስፋ ወደ ኋላ እንዲመለስ መፍቀድ አይገባም ነው ያሉት።

የሚገጥሙ ችግሮች ቢኖሩ እንኳ ሀገርን ከፊት በማስቀደም በውይይት ብቻ መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ይህን ኃላፊነት መወጣት ደግሞ ለተወሰነ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የእያንዳንዱን ዜጋ ሚና የሚጠይቅ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም