ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል-- ዶክተር አረጋዊ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል-- ዶክተር አረጋዊ
አዲስ አበባ መጋቢት 24/2013/ኢዜአ/ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በብዙ ችግሮች ውስጥ እያለፈ የህዝቡ ተሳትፎም ተጠናክሮ ቀጥሎ በጥሩ አፈፃፀም ላይ የሚገኝ መሆኑን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅ/ ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ተናገሩ።
ህይወት በውሃ ትቆም ዘንድ የምድር 1/3ኛው ክፍል በውሃ ተሸፍኖ ይገኛል።
ምድር ከለገሰቻቸው የውሃ ጅረቶች መካከልም ረጅሙ የአባይ ወንዝ በርካታ አገሮችን አቆራርጦ ያልፋል።
ውሃው በርካታ አገራትን አቆራርጦ ቢያልፍም የግብፅን ያክል እንዳሻው የሚጠቀመው ሀገር ግን እስካሁን የለም።
የወንዙ 86 በመቶ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያም የአባይ ውሃ የበይ ተመልካች እንጂ ተጠቃሚ ሳትሆን ለዘመናት ዘልቃለች።
ከወንዙ ኤሌክትሪክ ማግኘት እየተቻለ 60 ከመቶ በላይ ህዝቧ አሁንም ጨለማ ውስጥ ይኖራል።
ሆኖም ኢትዮጵያ በርከት ያሉ ዜጎቿን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ በማድርግ ከጨለማ ለማላቀቅ እንዲሁም ከሌሎች ሀገሮች ጋር በጋራ ለመጠቀም በማሰብ የግድብ ግንባታን ጀምራለች።
"የግድቡ መሃንዲሶች እኛው፤ ግንበኞችና ሰራተኞች እኛው፤ የፋይናንስ ምንጮችና አስተባባሪዎች እኛው" በሚል የሁሉም ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ያረፈበት አኩሪ ችቦም የተለኮሰው መጋቢት 24/2003 ዓ.ም ነበር።
ለግድቡ ግንባታ ሁሉም ከኪስ፣ ከመቀነቱ እያወጣ ግንባታውን አስቀጥሎ አሁን ላይ አፈፃፀሙ 79 በመቶ ደርሷል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረም ድፍን 10 ዓመታትን ሲያስቆጥር በሀገር ውስጥም በውጭም በርካታ ፈተናዎች ተፈራርቀውበታል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ፤ ግድቡ በተጀመረ ማግስት ጀምሮ የህዝቡ ተነሳሽነትና ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋል አደር ብሎ ግን ግልጸኝነት በጎደለው የህወሃት ኢህአዴግ መንግስት አሰራር ህዝባዊ ተሳትፎና ተነሳሽነቱ ቀዝቀዝ ብሎ እንደነበር ጠቁመዋል።
ለግድቡ ግንባታ የሚሰበሰበው ገንዘብም ለታለመለት ዓላማ ሳይውል ጥራት በጎደላቸው እና ተያያዥ ስራዎች ሰበብ ሲመዘበር መቆየቱን አስረድተዋል።
ከአገራዊ ለውጡ ማግስት ግን በግንባታ ሂደቱ ላይ የነበሩ ውስብስብ ችግሮች ታርመው ህዝቡ በግልጸኝነት የሚሳተፍበትን ሁኔታ በመፍጠር ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በታላቁ አገራዊ ፕሮጀክት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን በመቋቋም የግንባታ ሂደቱ በተሻለ አፈጻጸም ላይ ይገኛል ብለዋል።
ዜጎችም ስለ ጋራ ግድባቸው በኩራት የሚናገሩበትና በገንዘብ፣ በጉልበትና በእውቀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉበት የእድገት ደረጃ ስለመደረሱ አመላክተዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በግድቡ ዙሪያ ህዝቡ ያሳየው የአልበገር ባይነት ወኔና ቁጭት አገሪቱ በውስጥና በውጭ የገጠሟትን ችግሮች መቋቋም እንደቻለች አንስተዋል።
ከለውጡ ማግስት በግንባታ ሂደቱ ብልሹ አሰራር በመፍጠር የአገርና ህዝብን አደራ ትተው የራሳቸውን ኪስ ሲያደልቡ የነበሩ አካላትን ማጥራትና ማስወገድ እራሱን የቻለ ከባድ ስራ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከዓመታት በፊትም የግድቡን ቀጣይ ህልውና በሚፈታተን መልኩ ብቃት የሌላቸው ኮንትራክተሮችን ማሳተፍ፣ የተበላሹ ጥሬ እቃዎችን ማቅረብ እና ሙስና በግድቡ ላይ የተሰሩ ሸፍጦች እንደነበሩ ተናግረዋል።
አጠቃላይ በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ግድቡን በታለመለት ሁኔታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑ ዶክተር አረጋዊ አስረድተዋል።
ለግድቡ ግንባታው የሚውል ገንዘብ በማዋጣት ሂደት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵዊያን አስተዋጽኦም ታሪክ የሚዘነጋው አንዳለሆነ ጠቁመዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደካሁን በፊት ሁሉ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያድረጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአንድነት ምልክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታም አሁን ላይ 79 በመቶ የደረሰ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌትም በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ ይታወሳል።
ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከ15 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል።
በ2013 በጀት ዓመትም ለግድቡ ግንባታ 1 ነጥብ 5 ቢለየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገልጿል።