የግልና አካባቢ ንጽህና በመጠበቃችን ተላላፊ በሽታዎችን ተከላክለናል- ግንባር ቀደም ቤተሰቦች - ኢዜአ አማርኛ
የግልና አካባቢ ንጽህና በመጠበቃችን ተላላፊ በሽታዎችን ተከላክለናል- ግንባር ቀደም ቤተሰቦች

ጎባ መጋቢት 24/2013 /ኢዜአ/ በጤና ኤክስቴንሽን ትምህርት ባገኙት ግንዛቤ ታግዘው የግልና አካባቢ ንጽህናን በአግባቡ በመጠበቃቸው ያጋጥሟቸው ከነበሩ ተላላፊ በሽታዎች መከላከል መቻላቸውን በባሌ ዞን የሲናና ወረዳ ግንባር ቀደም ቤተሰቦች ገለጹ፡፡
በዞኑ ባለፉት ስምንት ወራት የግልና የአካባቢ ንጽህናን ጨምሮ 18ቱን የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆች ተግባራዊ ያደረጉ ከ14ሺህ የሚበልጡ ግንባር ቀደም ቤተሰቦች ተመርቀዋል።
በመርሀ ግብሩ ታቅፈው ባገኙት ግንዛቤ የግልና የአካባቢያቸውን ንጽህና በመጠበቅ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል መቻላቸውን ግንባር ቀደም ቤተሰቦቹ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በሲናና ወረዳ ኦቦራ ቀበሌ የሴቶች ልማት ቡድን መሪ የሆነችው ወይዘሮ ኡርጎ ተሾመ ከዚህ ቀደም የቤተሰብ አባሎቻቸው ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች በተደጋጋሚ ስለሚጋለጡ ላልተፈለገ የህክምና ወጪ ሲዳረጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ መርሃ ግብር ለሁለት ወራት በተሰጣቸው ስልጠና በግልና አካባቢ ጥበቃ፣ በመጸዳጃ ቤት አጠቃቀም፣ በህጻናት ክትባት፣ በተመጣጠነ ምግብ ዝግጅትና በመሳሰሉት በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ያገኙትን ግንዛቤ በግላቸውና በቡድን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ የቤተሰብ አባሎቻቸው በተላላፊ በሽታ የሚያዙበት አጋጣሚ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይም እንደ ጉንፋን የመሳሰሉ የመተንፈሻ አካል፣ ተውከትና ተቅማጥ፣ የአይንና ሌሎች በሽታዎችን መከላከል መቻላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
"በጤና ኤክስቴንሽን በሚሰጠው ስልጠና ላይ ከባለቤቴ ጋር በመሳተፍ ባገኘነው ግንዛቤ የግልና አካባቢ ንጽህናችንን በመጠበቅ ከተላላፊ በሽታዎች እራሳችንና ቤተሰባችንን ለመታደግ ችለናል" ያሉት ደግሞ የወረዳው ግንባር ቀደም ወይዘሮ ከዲጃ አህመድ ናቸው።
ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ያጋጥሙ የነበሩና ከንጽህና ጉድለት ይከሰቱ የነበሩ የህጻናት በሽታዎችና ሌሎች የጤና ችግሮች ዛሬ ላይ መቃለላቸውን ተናግረዋል።
"በስልጠና ያገኘነውን ግንዛቤ ተግባራዊ በማድረጋችን የእኛና የጎረቤቶቻችን ጤና እያተሻሻለ ይገኛል’’ብለዋል።
የሲናና ወረዳ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ አብደላ እንደገለጹት በወረዳው በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካኝነት ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው መርሃ-ግብር የህብረተሰቡ የጤና አጠባበቅና አመለካከት እየተሻሻለ መጥቷል።
የግልና አካባቢ ንጽህናን ጨምሮ ሌሎች የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በግላቸው ተግባራዊ የሚያደርጉ ቤተሰቦች እየተበራከቱ መምጣቸውን ገልጸዋል።
የባሌ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሴይፈዲን መሐመድ በበኩላቸው “መንግስት በሽታን መከላከል ላይ ያተኮረ ህብረተሰብን ማዕከል ያደረገ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ ነው” ብለዋል፡፡
በተለይም የግልና አካባቢ ንጽህናን ተግባራዊ በማድረግና መሰረታዊና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የሴቶች የልማት ሰራዊት ሚና የላቀ መሆኑን አመልክተዋል።
በዞኑ ባለፉት ስምንት ወራት መርሀ ግብሩን በተሻለ ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ግንባር ቀደም የሆኑ ከ14 ሺህ የሚበልጡ ቤተሰቦች መመረቃቸውን አስታውቀዋል።
ግንባር ቀደም ቤተሰቦቹ የግልና የአካባቢ ንጽህናን፣ የተመጣጠነ ምግብ ዝግጅትን፣ የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀምን ጨምሮ ሌሎች 18ቱን የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረጋቸው መመረቃቸውን ተናግረዋል።
"የቤተሰቦቹ ለምረቃ መብቃት የመርሀ ግብሩን ስኬታማነት አመላካች ነው" ብለዋል።
በባሌ ዞን ከ182 ሺህ የሚበልጡ በመውለድ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች መኖራቸውን የዞኑ ጤና ጥበቃ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን መርሀ ግብር መሰረታዊ ፍልስፍና በሰለጠኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት የጤና መልዕክቶችና ተግባራት ወደ እያንዳንዱ ቤትና ቤተሰብ በማድረስ የህብረተሰቡን ንቃተ ጤና በማሳደግ ጤናማ ማህበረሰብ መፍጠር ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የጤና መረጃ እንደሚያሳየው በሀገራችን በህይወት ከሚወለዱ 1ሺህ ህጻናት 64 ቱ አምስት ዓመት ሳይሞላቸው በቀላሉ ልንከላከለውና ልናክመው በምንችለው የጨቅላ ህጻናት የጤና ችግር በሆኑ ሳንባ ምች፣ ተቅማጥ፣ ወባ፣ ኩፍኝና ምግብ እጥረት ችግሮች ህይወታቸው ያልፋል፡፡