የዉሃ ሀብቶቻችን ለአገራዊ ኢኮኖሚያችን ጥሪት የመሆን እምቅ አቅም አላቸው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ - ኢዜአ አማርኛ
የዉሃ ሀብቶቻችን ለአገራዊ ኢኮኖሚያችን ጥሪት የመሆን እምቅ አቅም አላቸው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ
መጋቢት 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የዉሃ ሀብቶቻችን ለሀገራዊ ኢኮኖሚያችን ጥሪት የመሆን እምቅ አቅም አላቸው” ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰረተ ድንጋይ የተጣለበትን 10ኛ ዓመትን አስመልክተው የ”እንኳን አደረሰን” መልዕክት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም “አገራችን ኢትዮጵያ ከታደለቻቸው ጸጋዎች መካከል የዉሃ ሀብታችን አንዱና የእድገታችን መሠረት ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ “ከነዚህ የዉሃ ሀብቶቻችን መካከል ደግሞ አባይና ገባሮቹ፣ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያችን ጥሪት የመሆን ታላቅ እምቅ አቅም አላቸው” ብለዋል፡፡
እምቅ አቅሙ ቢኖርም በአገራዊ የአቅም ውስንነትና የዓለም ዓቀፍና ቀጣናዊ አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሳ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቶቿ የመልማት ምኞቷ ተገድቦ መቆየቱን አስታውሰዋል።
“አባይ የአገራችን ሁለት ሶስተኛ የገጸምድር ውሃ ሃብት የሚገኝበት ተፋሰሳችን ነው” በማለት ገልጸው፤ ይህን ተፋሰስ ማልማት ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
“በመሆኑም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ገንብተዉ ለዚህ ያደረሱትና ተስፋቸውን ያሳደሩበት አንጡራ ሀብታቸው ነው” ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ ስኬት ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ ዉጣ ዉረዶችንና ፈተናዎችን በማለፍ የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት መፈጸሙን አስታውሰው፤ ሁለተኛውን ሙሌት በመጪው ክረምት ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ ፕሮጀክት የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮችም ከጎርፍ እና ድርቅ ከመሳሰሉት አደጋዎች እንደሚጠበቁ ገልጸው፤ በተለያየ መንገድም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
“አባይን የመጠቀም ጉዳይ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ የሕይወትና የሉዓላዊ ክብር ጉዳይ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ “ኢትዮጵያ ተፋሰሱን ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በጋራ እንጠቀም ስትል ለጎረቤቶቿ ዳግም ጥሪዋን ታቀርባለች” ብለዋል።
ወቅቱ በጋራ መቆምና አንድነት ማሳየት የግድ የሚልበት መሆኑን ተናግረው፤ “በዚህ ዓመት ለህዳሴ ግድብ የታየዉ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል” ብለዋል፡፡
ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከአንድ ቢልየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉ የሕዝቡን ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚያረጋግጥ ጠቅሰው፤ ምስጋና አቅርበዋል።
“ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከመጀመርያዉ አንስቶ ሌት ተቀን፡ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ለለፉ፣ አመራር ለሰጡ፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት ይህን የግድባችንን አስረኛ ዓመት አከባበር ላዘጋጁ ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ” ብለዋል።
“ይህ ቀን የጀመርነውን ለመጨረስ የገባነውን የትውልድ ቃል ኪዳን የምናድስበት እንደሚሆን እምነቴ ነው” ሲሉ ገልጸው፤ “ይህንና ሌሎች ግዙፍ ተአምሮችን የሠራን እኛ ኢትዮጵያዉያን ስንተባብር፣ ስንቻቻል፣ ለማይተካዉ የሰዉ ልጅ ሕይወት የሚገባዉን ክብር ስንሰጥ ነዉ የምንወዳት አገራችንን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ዳግም ተአምር ልንሠራ የምንችለዉ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።