ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ ተራራማ ቦታዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ ነው -የከተማው አስተዳደር

ጎንደር መጋቢት 24/ 2013 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ተራራማ ቦታዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ የፕሮጀክት ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቁ፡፡

ተራራማ ቦታዎችንና ዘመናዊ ፓርኮችን ለመገንባትና ለማስፋፋት የሚያስችል የ21 ሚሊዮን ብር የዲዛይን ስራ እየተካሄደ መሆኑ ተመልክቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ  ለኢዜአ እንደተናገሩት  በከተማው  በተለምዶ  ጎሃ ገነትና ወንፊት ተራራ የተሰኙ አካባቢዎችን  የቱሪስት መዳረሻ  ለማድረግ  እየተሰ ነው።

በተራራማ ቦታዎቹ 20 ኪሎ ሜትር የሸፈነ የእግረኛ፣ የብስክሌትና የተሸከርካሪ መተላለፊያ መንገዶች ግንባታ እንደሚካሄድ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ በሆነው በጎሃ ተራራ የ4 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ለማከናወን የዲዛይን ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

ዘመናዊ የመዝናኛ ሎጆችን፣ ባለ ኮከብ ሆቴሎችን ጨምሮ ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመገንባት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች ቦታዎቹን በጨረታ ለማስተላለፍ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

ታላላቅ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በአላት የሚከበሩበትን የከተማውን መስቀል አደባባይ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

አደባባዩን የስፋትና በውስጡ ለቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ ሙዚየሞች፣ የባህል አልባሳትና የእደ ጥበብ ውጤቶች መሸጫ ሱቆች ግንባታዎች እንደሚካሄዱ አመላክተዋል።

በተለምዶ ፖሊስ ሜዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢም ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የቱሪስት መዝናኛ መናፈሻ ፓርክ የሚገነባ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ፓርኩ በውስጡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ጨምሮ የመዝናኛና የቤተ-መጻህፍት  አገልግሎቶችን አሟልቶ የሚገነባ በመሆኑ ለወጣቱ የመዝናኛና የእውቀት መገንቢያ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

ለተራራ ልማቱ የዲዛይን ስራም 21 ሚሊዮን ብር የከተማ አስተዳደሩ መድቦ ወደ ስራ መግባቱን አውስተዋል።

"የፕሮጀክቶቹ የግንባታ ወጪ በጥናት ከተለየ በኋላ በከተማ አስተዳደሩ፣ በክልሉ መንግስትና በአለም ባንክ የበጀት ድጋፍ ስራው ይጀመራል" ብለዋል፡፡

"የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎቹ የዲዛይን ስራ የከተማውን ማስተር ፕላን በጠበቀ መንገድ ይከናወናል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን፣ ዲዛይንና  ቁጥጥር  ስራዎች  ኮርፖሬሽን  ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ነገደ አባተ ናቸው፡፡

ጎንደር ከተማ ታሪካዊና ጥንታዊ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ እንደመሆኑዋ የዲዛይን ስራው ታሪካዊ አሻራውን ግምት ውስጥ በማስገባት በጥራትና በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ኮርፖሬሽኑ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም