ቀጥታ፡

በንጹሐን ላይ ጥቃት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የማያዳግም ህግ የማስከበር ስራ ሊከናወን ይገባል...አቶ አገኘሁ ተሻገር

ባህር ዳር /ኢዜአ/ መጋቢት 23/2013 ማንነትን መሰረት በማድረግ በንጹሐን ላይ ላይ ጥቃት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የተጠናከረ የህግ ማስከበር እርምጃ እንዲወስዱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር  አገኘሁ ተሻገር ጠየቁ።
ርዕሰ-መስተዳደሩ ዛሬ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ማንነትን መሰረት በማድረግ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ንጹሐን እየሞቱና እየተፈናቀሉ ይገኛሉ።

የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ችግሩን ለማስቆም እየሰሩ ቢሆንም እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ ባለመምጣቱ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የተጠናከረ ህግ የማስከበር ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ጽንፈኛ ኦነግ ሸኔና የጉሙዝ አማጺ ቡድን በህጻናት፣ ሴቶችና ንጹሐን ላይ የሚፈጽመውን የጭካኔ ድርጊት እንደሚያወግዝ ገልጸው ችግሩን ለመፍታት ከሚሰሩት የፌዴራልና የየክልሎቹ መንግስታት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።

“ክልሎች ይሔ ችግር እንዳይከሰት ከፍተኛ ስራ እንደሚሰሩ እናውቃለን” ያሉት አቶ አገኘሁ ነገር ግን ጉዳቱ ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሰ ለመምጣቱ በቅርቡ በሆሮጉድሩ ወለጋ በመተከልና በሌሎች ቦታዎች ያጋጠሙ ጥፋቶችን ጠቅሰዋል።

“ይሄ የጥፋት ሃይል እያደረሰ ያለውን ዜጎችን የማፈናቀልና የመግደል ተግባር ለማስቆም የፌዴራል የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የማያዳግም እርምጃ እንዲወስዱ በአማራ ክልል ህዝብና መንግስት ስም ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦችና ክልሎችም ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ጉዳት እየደረሰበት ካለው ህዝብ ጎን በመቆም ለጋራ ሃገርና ለሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም