ቀጥታ፡

የእምነት ተቋማት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመቀነስ አስገዳጅ የመከላከል መመሪያዎችን እንዲተገብሩ ተጠየቀ

መጋቢት 23/2013 ( ኢዜአ) የእምነት ተቋማት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመቀነስ አስገዳጅ የመከላከል መመሪያዎችን እንዲተገብሩ ተጠየቀ።

የኮቪድ-19 ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የጤና ሚኒስቴር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ በመግለጫው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በየቤተ እምነቱ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው የኮቪድ መከላከል ጥንቃቄ እየተተወ መጥቷል።

ብዙ ሰዎች የሚገኙባቸው ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትም ያለ ማስክ እና ያለ በቂ አካላዊ ርቀት እየተከወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።“ወረርሽኙ የለም” በማለት የተሳሳተ መልእክት የሚያስተላልፉም አሁን ላይ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የጥንቃቄ መልእክቶችን ማስተማር አለባቸው ብለዋል።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን መጠቀም፣ አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ እና ቤተ እምነቱ ከሚቀበለው አቅም አንድ አራተኛውን ብቻ ማስተናገድ እንዲችሉ መመሪያ መሰጠቱን ገልፀዋል።

ለቫይረሱ መዛመት የሚዳርጉ የጥንቃቄ ጉድለቶችን በማስተካከል የእምነት ተቋማቱ አስገዳጅ መመሪያዎችን እንዲተገብሩ ጥሪ ቀርቧል።የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ ከቫይረሱ ራስን ለመጠበቅና አሁን የደረሰበትን አሳሳቢነት በመረዳት የሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎችን በሙሉ መተግበር ይገባል ብለዋል።

ክትባቱን ከመውሰድ ጋር ተያይዞም ያለውን የተዛባ አመለካከት ማስተካከል ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።ሌሎች ተቋማትና የማህበረሰብ ክፍሎችም የተቀመጡ ክልከላዎችን ሙሉ ለሙሉ እንዲተገብሩ የማድረግ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።

በትራንስፖርት፣ በትምህርት፣ በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ በገበያ ቦታዎች፣ በካፌና ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎች፣ መዝናኛ ቦታዎች፣ ህዝባዊ ስብስብ እና ስፖርታዊ ክንውኖች በሚደረጉባቸው ስፍራዎች ላይ ቁጥጥሩ እንዲቀጥል ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

የኮቪድ-19 ክትባትን በሚመለከት ለጤና ባለሙያዎች እና በጤና ተቋማት ለሚሰሩ መስጠት እንደተጀመረ የሚታወቅ ሲሆን ከመጪው ሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች መስጠት ይጀመራል ብለዋል።

በአገሪቱ ለጽኑ ህሙማን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የኦክስጅን አቅርቦት እጥረት የነበረ መሆኑን ገልጸው ይህንን አቅርቦቱን ለማስፋት በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሰራ ቆይቷዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም