የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 50ኛ የወርቅ ኢዮቤልዩ ውድድር የፊታችን ማክሰኞ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 50ኛ የወርቅ ኢዮቤልዩ ውድድር የፊታችን ማክሰኞ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 50ኛ የወርቅ ኢዮቤልዩ ውድድር የፊታችን ማክሰኞ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ውድድሩ በቶኪዮ ኦሊምፒክ እና በአልጀርስ ለሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመምረጥ ያግዛል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ50ኛው የወርቅ ኢዮቤልዩ ውድድር ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንደገለጹት ሻምፒዮናው በጃፓን ቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመምረጥ ያግዛል።
በተለይ እኤአ ከሰኔ 1 እስከ 5 ቀን 2021 በአልጄሪያ አልጀርስ ለሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመምረጥ ይረዳል ነው ያሉት።
በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በክለቦችና በማሰልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር እድል ለመፍጠር እንደሚረዳና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትም እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።
ውድድሮቹም ከ800 እስከ 10 ሺህ ሜትር፣ 3ሺህ ሜትር መሰናክልና እና የእርምጃ ውድድርን እንደሚያካትት አቶ ቢልልኝ ገልጸዋል።
"ውድድሩ 50ኛ ዓመቱን በመያዙ የተለየ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ይኖረዋል "ያሉት
አቶ ቢልልኝ ሽልማቱ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ የሚወጡትን ተወዳዳሪዎች ሊያሸልም ይችላል ብለዋል።
በግልና በቡድን ለሚያሸንፉ፣ ለኮከብ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች እና ዳኞችም እንደየደረጃቸው ሽልማት እንደሚኖር ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት 49ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮቪድ-19 ምክንያት ሳይካሄድ የቀረ ሲሆን በ48ኛው ሻምፒዮና በሴቶች መከላከያ በወንዶች ኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ ደግሞ መከላከያ ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1963 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዘንድሮ ሻምፒዮና 507 ሴቶችና 736 ወንድ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።