ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝቡ ያሳየው ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

አዲስ አበባ  መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝቡ ያሳየው ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

ጽህፈት ቤቱ የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 10ኛ አመት አስመልክቶ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል።

ኢትዮጵያዊያን ባለፉት አስርት አመታት ግድቡን ለመገንባት አንድ በመሆን ላሳዩት ቁርጠኝነትም አድናቆቱን ገልጿል።

በመሆኑም የግድቡን ግንባታ በስኬት ለማጠናቀቅ ህዝቡ ያሳየው ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።

በግንባታ ሂደቱና በሶስትዮሽ ድርድሩ ያጋጠሙትን አያሌ ፈተናዎች በማለፍ ዛሬ ላይ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥ፣ በልገሳና ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶች ሲሰራ ቆይቷል ብሏል ፅህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫው።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 79 በመቶ በመድረሱን ጠቅሶ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መከናወኑንም አስታውሷል።

የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መከናወኑን ተከትሎ በ9 ወራት ብቻ በከፍተኛ መነሳሳት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ከህዝቡ መሰብሰብ መቻሉንም ጠቅሷል።

በያዝነው አመትም 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌትና የመጀመሪያ የሃይል ማመንጨት የሙከራ ስራ ለማከናወን የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታን ማጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ ህልውና እና ሉአላዊነት ወሳኝ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።

ፅህፈት ቤቱ በመግለጫው "ጤናችን ይጠበቃል!፤ ግድባችንምይጠናቀቃል!" በማለት የህዝቡ ድጋፍና እግዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም