ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ገደብ በሥራችን ላይ ተፅእኖ አሳድሯል- ነጋዴዎች

አዲስ አበባ  መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ገደብ በሥራችን ላይ ተፅእኖ አሳድሯል ሲሉ አንዳንድ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ ገደቡ ጤናማ የገንዘብ አጠቃቀም እንዲኖር ታስቦ በመሆኑ አሳማኝ ምክንያት ይዘው የሚጠይቁ ተቋማትና ድርጅቶች ይስተናገዳሉ ብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ባንኩ ባወጣቸው ሶስት መመሪያዎች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት፣ አምራቾች፣ ላኪዎችና የኮንስትራክሽን ሴክተር ተወካዮች ጋር ተወያይቷል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው እንዳሉት ምክር ቤቱ ንግድና ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ ፖሊሲዎችና ሕጎች ሲወጡ የግሉን ዘርፍ ጥቅምና ፍላጎት ባስጠበቀ መልኩ መሆኑን ማረጋገጥና በዚያም ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር አንዱ ተግባሩ ነው፡፡

ባንኩ ሰሞኑን ይፋ ባደረጋቸው መመሪያዎች ከአሰራርና ከአተገባበር ጋር ተያይዘው ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ከባንኩ ኃላፊዎችና ከግሉ ዘርፍ   ውይይት አዴሬጓል።

በውይይቱ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፤ ባንኩ በጥሬ ገንዘብ ላይ የጣለው የዝውውር ገደብ በሥራቸው ላይ ችግር ፈጥሯል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ባንኩ በአንድ ቀን ግለሰቦች ከባንክ የሚያወጠት ጥሬ ገንዘብ 50 ሺህ ብር፣ ድርጅቶችና ተቋማት ደግሞ 75 ሺህ ብር እንዲሆን መገደቡ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ይህም ጥሬ ዕቃዎች ለመግዛትና የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች የእጅ በእጅ ክፍያ ለመፈጸም አስቸግሯል ብለዋል።

በተጨማሪም በሣምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ብር ከባንኮች እንዳያወጡ የወጣው መመሪያም ሥራቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡

ከአካውንት ወደ አካውንት በሣምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ማዘዋወር እንዳይቻል የወጣው መመሪያም እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በውጪ ምንዛሪ የሚያስቀምጡት ገንዘብ ከቅንጦት ዕቃዎች ይልቅ፤ ለምግብና  ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች ማስገቢያ እንዲውል የወጣው መመሪያ ግን ጊዜውን የጠበቀና አግባብነት ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ፤ መመሪያዎቹ በአገሪቱ ጤናማ የገንዘብ ዝውውርና አጠቃቀም እንዲኖር ታስቦ መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቶችና ተቋማት በቀን በሚያወጡት ገንዘብ ላይ ገደብ የተጣለው ሕገ-ወጥ ተግባርን ለመከላከል እንጂ፤ ሕጋዊ  እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን ለመገደብ አይደለም ብለዋል፡፡

ሆኖም ሕጋዊ ሆነውና አሳማኝ ምክንያት ይዘው ለሚጠይቁ ተቋማትና ነጋዴዎች ከተቀመጠው ገደብ በላይ ጥሬ ገንዘብ እንዲሰጡ መፈቀዱንም  ምክትል ገዢው አስረድተዋል፡፡

ሕጋዊ መሰረት ያለው ንግድን ለማበረታታት ወደ ፊት ተጨማሪ መመሪያዎች ሊወጡ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጡትን ገንዘብ በምን ዓይነት አግባብ መጠቀም እንደሚኖርባቸው፣ አንድ ድርጅት ወይም ተቋም ከባንክ ውጭ መያዝ የሚችለውን የገንዘብ መጠን ለመወሰንና ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ቢዝነስና ተቋም የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም የሚወስን መመሪያዎች ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም