ቀጥታ፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ  መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ) የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ።

የሰላም ሚኒስትር የሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ኃላፊ አቶ አህመድ ሰኢድ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ድጋፉን ተረክበዋል።   

የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ክልል ህዝብን ለመደገፍና መልሶ ለመቋቋም "ከፍተኛ ጥረት" በማድረግ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የተደረገው ድጋፍም ተጨማሪ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።      

እስካሁን መንግስት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ጨምሮ ከ70 በመቶ በላይ በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ማድረሱን ጠቅሰዋል።   

ከሰብአዊ ድጋፎች በተጓዳኝ የጤና እና ሌሎች ድጋፎችም በስፋት እየተደረጉ መሆኑንም አክለዋል።

ከመንግስት ድጋፍ በተጨማሪ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዛሬ ያደረገው 47 ቶን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ ትልቅ እገዛ አለው ብለዋል።   

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል በፍጥነት ተጓጉዞ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ይደርሳል ብለዋል።    

"የኢትዮጵያ መንግስት ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ምስጋና ያቀርባል ያሉት" ሃላፊው ድጋፉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።      

በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል የተጎዱ አከባቢዎችን መልሶ ለመቋቋም በተለያዩ ዘርፎች በመንግስት ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑም አብራርተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም