የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጀመረውን ቅንጅታዊ አሠራር ሊጠናከር ይገባል- የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጀመረውን ቅንጅታዊ አሠራር ሊጠናከር ይገባል- የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ
መጋቢት 23/2013/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጀመረውን ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ2009 በጀት ዓመት እስከ 2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የካፒታል እቃዎች ኪራይ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን በተመለከተ ከባንኩ ኃላፊዎቸ ጋር ውይይት አካሂዷል።
በክዋኔ ኦዲቱ በባንኩ ሰራተኞችና ህብረተሰቡ በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤና ተመሳሳይ አሰራር እንደሌለ ተጠቅሷል።
ባንኩ ከውጭ የሚያመጣቸውን የካፒታል እቃ አስፈላጊውን የጉምሩክ ስነስርዓት ፈፅሞ ከወደብ ባለማንሳቱ ለኢንተርፕራይዞች ተጨማሪ ወጭና መጓተት ዳርጓል ተብሏል።
በግኝቱ እንደተመላከተው ባንኩ ዋናውን ብድርና የአገልግሎት ክፍያ ወለድ በወቅቱ እንዳልሰበሰበና የሊዝ ፋይናንሲንግ ተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞች በወቅቱ የሊዝ ኪራይ ብድር እንዲመልሱ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ተደርጓል።
የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት በአገሪቱ በቅርብ ዓመታት መሥራት የተጀመረ በመሆኑ ባንኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊያከናውን ይገባል ያሉት የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ ናቸው።
ባንኩ ከጉምሩክ፣ ክልሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን የቅንጅት ስራ ማጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ባንኩ የተሰጠውን ኃላፊነት ለማስፈፀምና የችግር ምንጮችን ለይቶ መስራት መጀመሩ መጠናከር ያለበት መሆኑ በቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል።
በተለይ ከክልሎች ጋር በመተባበር ካልሰራ ውጤታማ ስለማይሆን ቅንጅታዊ አሰራሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሀመድ የሱፍ አሳስበዋል።
የክዋኔ ኦዲት ግኝት ለማረም የድርጊት መርሃ-ግብር በማዘጋጀትና የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ለዋና ኦዲተር በአስቸኳይ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው በበኩላቸው በዋና ኦዲተር የተሰጠውን ግኝት እንደሪፎርም አካል በመውሰድ እየሰራ ነው ብለዋል።
የባንኩ አዲስ ማኔጅመንት በተያዘው አመት መስከረም ወር ላይ ሥራ መጀመሩን አንስተው ብልሹ አሠራሮችን በመፍታት ውጤት ማምጣቱንም አብራርተዋል።
ከጥቅምት እስከ የካቲት ባሉት ወራት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ከኮርፖሬት ደንበኞች ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገንዘብ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ይህ ሥራ የተሰራው ደንበኞች አገልግሎት እንዲያገኙ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው በመግለፅና ብድራቸውን ለሚከፍሉ ደንበኞችም ሊሻሻሉላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በፍጥነት መፍትሔ እንዲያገኙ በማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህን አሠራር በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለመተግበር እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢንተርፕራይዞችን ግንዛቤ ለማሳደግ 2 ሺህ 500 ለሚሆኑ አንቀሳቃሾች ሥልጠና መስጠቱንና በቀጣይም ሌሎች አዳዲስ ሊገቡ ያሰቡና ቅድመ ሁኔታዎችን እያሟሉ ላሉ ደንበኞች ሥልጠና እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን የቅንጅት ችግር ለመፍታት የባንኩ አመራሮች ከክልል አመራሮች ጋር በመወያየት ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮችን ያካተተ ስትሪንግ ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልፀዋል።