ቀጥታ፡

በጥሩ ስነ ምግባር የታነጸ ተውልድ በመፍጠር ሂደት የሃይማኖት መሪዎች ሚና ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ  መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በጥሩ ስነ ምግባር የታነጸ ተውልድ በመፍጠር ሂደት መሪዎችና ልሂቃን እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት ሚና ወሳኝ መሆኑን የፌዴራል የስነ-ምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

የፌዴራል የስነ-ምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን ስነምግባርን በመገንባት ሂደት ላይ "የሃይማኖት ተቋማት ሚና እና ወቅታዊ አገራዊ የስነምግባር ችግሮች" በሚል ርፅስ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ምክክር አካሂዷል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ፀጋ አራጌ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የአገሪቱ ህዝቦች መልካም መስተጋብር ያላቸው ቢሆኑም የትውልዱ የስነምግባርና የሞራል ግንባታ ግን ችግር እየተስተዋለበት ይገኛል።

በጥሩ ስነ ምግባር የታነጸ ተውልድ በመፍጠር ሂደት የኮሚሽኑ ጥረት እንዳለ ሆኖ የሃይማኖት መሪዎችና ልሂቃን እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ተግባር በቀጣይ አገራዊ መፍትሄ ለማዘጋጀትና ሚናን በመውሰድ ኃላፊነትን መወጣት እንዲቻል መድረኩ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።  

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ስነምግባር ያለው ዜጋ እንዲኖር በማድረግ አድሎና ሙስናን እንዲሁም በጥቅም መሳሳብን የሚፀየፍ ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ሰላምና ፍትህ የነገሰባት አገር በመገንባት ሂደትም ጉልህ ድርሻ አላቸው ነው ያሉት።

የተበላሸ አሰራርን ለማረምና ትውልዱን ለማነፅ አገሩን የሚወድ ዜጋ ሁሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

አብዛኛዎቹ የስነምግባር እሴቶች ከቅዱሳን መፃህፍት የመነጩ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ናቸው።  

በመሆኑም ታማኝ፣ ሀቀኛና እውነተኛ የሆኑና ስነምግባር የተላበሱ ዜጎችን ለመፍጠር የሃይማኖት ተቋማት ምዕመናኖቻቸውን ማስተማርና መገሰፅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የስነምግባር ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው እንዲሁም በስነምግባር ግንባታ የሀይማኖት ተቋማት ሚና በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ከፅሁፍ አቅራቢዎቹ መካከል መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል፤ በአገሪቱ ለተፈጠሩ ችግሮች የስነ-ምግባር ችግር አንዱ አባባሽ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

እርስበርስ መገዳደል፣ ተከባብሮ ችግር መፍታት አለመቻልና የመሳሰሉት የስነ-ምግባር ጉድለት ማሳያ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በመሆኑም መልካም ትውልድ በመገንባት ሂደት የሃይማኖት ተቋማት ተግተው ሊሰሩ ይገባል፤ መንግስትም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባዋል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለን ጨመሮ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎችና የሲቪክ ተቋማት ተወካዮችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም