አፍሪካዊያን በህዳሴ ግድብ የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት ሊቃወሙ ይገባል---ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካዊያን በህዳሴ ግድብ የምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት ሊቃወሙ ይገባል---ምሁራን
ሚዛን/ሆሳዕና መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ) አፍሪካዊያን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገውን የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነትን ሊቃወሙ እንደሚገባ የሚዛን ቴፒና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታወቁ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩን ስኬታማ ለማድረግ የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ምሁራኑ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በሚዛን ቴፒ ዩንቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ መምህር ሳሙኤል ዮሃንስ እንዳሉት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እየተደረገ ባለው የሶስትዮሽ ድርድር ውስጥ ጣልቃ በመግባት ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ ሀገራትን መቀበል አይገባም።
ጉዳዩ ከአቅም በላይ አለመሆኑን እያወቁ በራስ አቅም ከመፍታት ይልቅ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በመፍቀድ የምዕራባዊያንን አጀንዳ ሲያስፈጽሙ የሚታዩ የአፍሪካ ሀገራት መኖራቸውን የጠቀሱት መምህር ሳሙኤል "ይህ የበታችነትን ስሜትን ያንጸባርቃል" ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት መፈታት አለበት የሚል አቋም እንዳላቸው ምሁሩ ጠቁመዋል።
"የአፍሪካ ህብረት አቋም በመውሰድና የራሳችንን ጉዳይ በራስ እንፈታለን በሚል ወኔ ድርድሩ ከአፍሪካ እንዳይወጣ ማድረግ አለበት" ሲሉም ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ዶክተር ንጉስ በላይ “የአባይ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ ነው፤ በሌሎች የውጭ ሀገራት ጉዳይ ላይ አፍርካዊያን ጣልቃ እንደማይገቡ ሁሉ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ሌሎች ገብተው የፈለጉትን ሊያደርጉ አይችሉም” ብለዋል፡፡
"አፍሪካዊያን በአንድነት በመቆም መብታቸውን ማስጠበቅ እንጂ ጉዳያቸው ላይ ሌላ አካል እንዲወስን መፍቀድ የለባቸውም" ብለዋል።
“የራስን ጉዳይ በራስ መፍታት እየቻሉ የውጭ አካል ጣልቃ ገብነትን መፍቀድ በሌላ መንገድ ቅኝ መገዛት ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ግድቡ የጋራ ጥቅምን የሚያስገኝና የትኛውንም ሀገር የሚጎዳ አለመሆኑን ያስረዱት ዶክተር ንጉስ ለፖለትካ ፍጆታ እየተደረገ ያለውን ጫና አፍሪካዊያን መረዳት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
"አሁን የሚያስፈለገው ግድቡ ስልሚፈጥረው ውጤት ከሶስቱ ሀገራት ጋር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ብቻ መነጋገር ነው" ያሉት ምሁራኑ ስለ አባይ ማሳመን የአፍሪካዊያን እንጂ የምዕራባዊያን ጉዳይ አለመሆኑን ተናግረዋል።
"ምዕራባዊያን ሃሳብ በመጫንና በማስቀየር ለአፍሪካዊያን የውሳኔ ባለቤት የሚሆኑ ከሆነ በአካል ወረው ባይገዙም በእጅ አዙር ቅኝ እየገዙ መሆናቸውን ተገንዝቦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የኛ ጉዳይ ነው በማለት የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን መያዝ አለበት" ብለዋል ምሁራኑ።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተመስገን ቶማስ በበኩላቸው "የግብጽና ሱዳን እኛ ብቻ መጠቀም አለብን የሚለው የራስ ወዳድነት እሳቤ በአሁኑ ዘመን የሚያዋጣ አይደለም" ብለዋል።
የሶስትዮሽ ድርድሩ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ፣ የሌሎች ሀገራት ጣልቃ ገብነት የሌለበትና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መፈጸም ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ግብጽና ሱዳን በድርድር መድረክና ከድርድሩ ዉጪ እያንጸረቁ የሚገኘው ሀሳብ ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀም ከማድረግ በተጨማሪ ትልሟን ለማቀጨጭ ያለመ በመሆኑ የድርድሩ ስኬታማ መሆን እንደማይታያቸውም ተናግረዋል።
ምሁሩ አክለውም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩን ስኬታማ ለማድረግ የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ዲንና መምህር አሳልፈው አበራ በበኩላቸው የግድቡ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ማከናወንና ግድቡ እንዲጠናቀቅ መላውን ህዝብ የማሳተፍ ስራ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በግብጽና ሱዳን እየተስተዋለ የሚገኘው እኔ ብቻ ተጠቃሚ ልሁን ራስ ወዳድነት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ የኢትዮጵያዊያን ተባብሮ ግድቡን ማጠናቀቅ የመደራደር አቅምን ከፍ ማድረግ እንደሚያስችል አስታውቀዋል።