በምርጫው ሂደት ፖለቲከኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች ከግጭት ቀሳቃሽ ድርጊቶች ሊታቀቡ ይገባል- ታዋቂ ግለሰቦች - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው ሂደት ፖለቲከኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች ከግጭት ቀሳቃሽ ድርጊቶች ሊታቀቡ ይገባል- ታዋቂ ግለሰቦች
አዲስ አበባ መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ)በምርጫው ሂደት ፖለቲከኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች በህዝቡ ዘንድ ግጭትና ቁርሾ ከሚፈጥሩ ድርጊቶች ሊጠነቀቁ እንደሚገባ ታዋቂ ግለሰቦች ተናገሩ።
የዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲካሄድም ዜጎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ደራሲ ጌታቸው በለጠ፣ አርቲስት ቻቺ ታደሰ እንዲሁም የሃይማኖት መምህሩ መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ አንዳሉት ለምርጫው ሂደት ሰላማዊነት በተለይ ተፎካካሪ ፖለቲከኞች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በምርጫው ሂደት ፖለቲከኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች በህዝብ ዘንድ ቅሬታ፣ ግጭት ወይም አለመግባባት ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮችና ፅሁፎች መታቀብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ፖለቲከኞች የሚፎካከሩት አገርን ለመምራትና ህዝብን ለማገልገል በመሆኑ ግጭትና አለመረጋጋት ከተፈጠረ ግን ምርጫው ትርጉም ያጣል ነው ያሉት።
በመሆኑም ፖለቲከኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና ሌሎችም ፅሁፎችና ንግግሮቻቸው የተመረጡና የተጠኑ፤ የህዝብና የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የማይጥሉ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።
ዜጎችም ለሀገር ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ለምርጫው ሰላማዊነት የድርሻቸውን አንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በተለይ በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚሰራጩ ሃሰተኛ መረጃዎች የምርጫ ሂደቱን ለማስትጓጎል በመሆኑ ማህበረሰቡ ይህንን ቀድሞ በመገንዘብ ትክክለኛ መረጃዎችን ከትክክለኛ የመረጃ ማሰራጫዎች መጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል።
ህዝቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የሚያገኝባቸውን አማራጮች ማስፋትና በወቅቱ ማድረስም ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ሃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።
ማህበራዊ ሚዲያ በእንደ ኢትዮጵያ ላሉ የነቃና ምክንያታዊ ማህበረሰብን ላልፈጠሩ ታዳጊ አገሮች የግጭት አቀጣጣይ በመሆኑ ጥንቃቄ ያሻዋልም ነው ያሉት።
ምርጫውን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና አገሪቱን ለማተራመስ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ አካላት ስላሉ ህዝቡ በጋራ ሊመክታቸው ይገባል ብለዋል።
ምርጫውን በተመለከተና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን ህዝቡ ማግኘት የሚገባው ከታማኝ ምንጮች እንጂ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ከሚያሰራጩ አካላት መሆን እንደሌለበትም መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ በበኩላቸው መንግስት ሃላፊነቱን ሲወጣ ህዝቡም ለሰላምና አንድነት በጋራ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ደራሲ ጌታቸው በለጠ እንዳሉትም በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሀገርና የትውልድ ሃላፊነት እንዳለባቸው ሊረዱ ይገባል።
መጋቢ ሐዲስ እሸቱ በበኩላቸው ሰዎች በሀገራቸውና ህዝባቸው ላይ ነገ ሊፀፀቱበት የሚችሉትን ድርጊት ከመፈፀም ቆም ብለው ማሰብ የኖርባቸዋል ነው ያሉት