እየበሰለ ያለ ፍሬ - ኢዜአ አማርኛ
እየበሰለ ያለ ፍሬ
በብርሃኑ አለማየሁ /ኢዜአ/
የሰው ልጆች በማኅበራዊ መስተጋብራቸው፣ በፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ሩቅ አስበው በሚያከናውኗቸው ስራዎች ለትውልድ የሚተርፍ አሻራ ያኖራሉ።
ከቀደምት የምድር መንግሥታት መካከል ስሟ ከፍ ብሎ የሚታየው ኢትዮጵያ አያሌ ዘመናትን የተሻገሩ የስልጣኔ አሻራዎች ካሏቸው አገሮች መካከል ግንባር ቀደም መሆኗን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ከሰሜን ጫፍ እስከ ምዕራብ ከደቡብ እስከ ምስራቅ ድረስ በቀደሙ አባቶች፣ በፖለቲካ መሪዎችና በሀይማኖት ተቋማት የተሰሩ ታሪካዊ አሻራዎች ዛሬ ላለነው ከታሪክ ቅርስነት አልፈው ሰፊ የስራ እድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት አንዱ የምጣኔ ሃብት ምሰሶ ሆነዋል።
ትውልድ የአባቶቹን እግር በተካ ቁጥር የራሱን አሻራ አስቀምጦ ማለፉ ደግሞ የዘመን ዑደት አካል ነው።
የዚህ ዘመን አሻራ ሆነው ከሚተላለፉ ህያው ቅርሶች መካከል አንዱና የኢትዮጵያውያን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ለድርድር የማይቀርበው “ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ” ነው።የግድቡ ግንባታ ይፋ የተደረገበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ለኢትዮጵያውያን የድል ቀን የተስፋ ብርሃን የመነጨበት ነበር።
ሚያዝያ ላይ የተጀመረው የግድቡ ግንባታ ላለፉት አስር አመታት በአገርና በህዝብ ሃብት የሚካሄድ ብሔራዊ ፕሮጀክት በመሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ሆኗል።
ለአስር ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ተደርጎበት እተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የግንባታው ከሦስት አራተኛ በላይ የሚሆነው ክፍል መጠናቀቁን መረጃዎች የሳያሉ።
በቅርቡ የወጣው የግድቡ ግንባታ ሂደት መረጃ 79 በመቶ ያህል መጠናቀቁን አመልክቷል።ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት የግንባታ ጊዜ የተያዘለት ግድቡ በተለያየ ምክንያት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አልቻለም።ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል የኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ሥራዎች መዘግየትና ከሲቪል ሰራተኞች ጋር የተያያዙ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በተጠቀሱትና በሌሎች ተያያዥ ነገሮች ምክንያት ለተወሰኑ አመታት የተቋረጠ በሚመስል መልኩ የዘገየው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከአገራዊ ለውጡ መምጣቱን ተከትሎ ከሶስት ዐመታት ወዲህ በተከናወኑ ተግባራት የመጀመሪያው የግድቡ የውሃ ሙሌት ተካሂዷል።
ባለፉት 10 ዓመታትም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ 14 ነጥብ 98 ቢሊዮን ብር ከህዝብ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
የግድቡ የውሃ ሙሌት የፈጠረው መነቃቃትና ከ2010 ጀምሮ የታዩ ከፍተኛ የቦንድ ግዢዎች የህዝባዊ ተሳትፎውን ከማነቃቃት አልፎ የግድቡን ኃይል የማመንጫ ቀን ተናፋቂ አድርጎታል።
ዘንድሮም በግድቡ አስረኛ ዓመት በመጪው ክረምት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንደሚካሄድ ይታወቃል። ለዚህም ውሃው የሚተኛበት ቦታ ተለይቶ ምንጣሮ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል።
የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ ለመድረስ ጫፍ ላይ እየደረሰ መጥቷል፤ ከግድቡ ብርሃን የሚመነጭበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ የተረዳንበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ኢትዮጵያም እየበሰለ ያለውን የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፍሬ የምትበላበት ዋዜማ ላይ ደርሳለች።