ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ህዝባዊ ተሳትፎው ይበልጥ ሊነቃቃ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ

አርባ ምንጭ ፤መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሀገሪቱን ዕድገት ለማስቀጠል ዓይነተኛ መሣሪያ በመሆኑ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ህዝባዊ ተሳትፎው ይበልጥ ሊነቃቃ እንደሚገባው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተናገሩ።

ለግድቡ ግንባታ ባለፉት ዓመታት 15 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያዊያን ድጋፍ መገኘቱን  የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት መገኘቱን አስታውቋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ግድቡ  በሃገሪቱ  ታሪክ ከተገነቡ መሠረተ ልማቶች ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን  የሚፈታ አውራ  ፕሮጀክት ያደርገዋል።

በተለይ በኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብና በራሳችን ባለሙያዎች የሚገነባ መሆኑ በህዝቡ መካከል የአብሮነትንና የይቻላል መንፈስን የፈጠረ ታላቅ ፕሮጀክት  ነው ብለዋል።

ተጠናቀቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም  የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ወደር እንደሌለው ገልጸዋል።

ግድቡ የዜጎችን በራስ የመተማመን መንፈስ ከማጠናከር ባለፈ የህዝቡን  ተጠቃሚነትና  አንድነት ይበልጥ የሚያስተሳሰር መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የግድቡ መሠረተ ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ድርሻውን በመወጣት የባለቤትነት ስሜት እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው ቀሪ የግንባታ  ሥራዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ  የህዝቡን ተሳትፎ  ይበልጭ መነቃቃት እንዳለበት ተናግረዋል።

መንግስት ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በርካታ የዲፕሎማሲ ስራዎች ሲከናውን መቆየቱን  የጠቆሙት ዶክተር ዳምጠው፤ በተለይ ምሁራን ከዓለም  አቀፍ የተፈጥሮ  ሀብት አጠቃቀም ህግ አንፃር የመጠቀም መብታችንን በማሳየት የበኩላችንን ልንወጣ  ይገባል ብለዋል።

ግድቡ በአፍሪካ ትልቁ የሃይል ማመንጫ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር ኢኮኖሚያዊና ቀጠናዊ ትስስር የሚፈጥር ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው  የምጣኔ ሀብት ትምህርት  ክፍል  ረዳት ፕሮፌሰር  መብራቱ ዓለሙ ናቸው።

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪውና  አምራች ዘርፎች  ትልቅ እመርታ እንድታስመዘግብ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ  ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከድህነት የመውጣቷ ጉዳይ የሞት ሽረት እንጂ በጥንት ታሪክ ብቻ መኖር አትችልም ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስራም በታቀደው አግባብ መሞላት እንዳለበት አመልክተዋል።

ግብፆች የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የአሜሪካና የአውሮፓ ጣልቃ ገብነት ቢሹም ኢትዮጵያ ባደረገችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ድርድሩ በአፍሪካ እንዲሆን የያዘችው አቋም ተገቢ መሆኑንም አስረድተዋል።

መቼም ቢሆን  የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን መፈታት እንዳለበት ጠቅሰው የሦስትዮሽ ድርድሩ ከአፍሪካ ፈፅሞ መውጣት የለበትም ብለዋል።

የህዳሴን ግድብ ጥቅም ላይ ማዋል ኢትዮጵያ ለዘመናት የተነጠቀችውን የአባይን ወንዝ የመጠቀም መብት ከማረጋገጥ በላይ የስራ አጥነትና ድህነት ችግሯን ለመፍታት እድል እንደሚፈጥርላት ገልጸዋል።

ለዚህ እውን መሆኑ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር የነበረው የህብረተሰቡ ተሳትፎና መነሳሳት ዳር እስኪደርስ ድረስ በተነቃቃ መንፈስ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ተአምር በበኩላቸው ግድቡ የአንድነትና የሉዐላዊነታችን መገለጫ በመሆኑ የህዝቡ  ተሳትፎ ተጠናክሮ  መቀጠሉን   ገልጸዋል።

ባለፉት አስር ዓመታት ከኢትዮጵያዊያን 15 ቢሊዮን ብር መገኘቱን  አስታውቀዋል።

በግብፅና ሱዳን በኩል እያጋጠመን ያለውን ተፅዕኖ ለማክሸፍ መንግስት በመደበኛው ዲፕሎማሲ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ወይዘሮ ፍቅርተ ገለፃ  86 በመቶ የአባይ ወንዝ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ጫና ለመቋቋም የተቻለውን ድጋፍ በማድረግ የሀገር አምባሳደር መሆን ይጠበቅበታል።

 አሁን ላይ የግድቡ ግንባታ በታቀደው መሠረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትና ሃይል የማመንጨት ስራም ተፈጻሚ እንዲሆን  ህዝቡ አንድነቱንና ሰላሙን በመጠበቅ በእኔነት ስሜት እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።

በቤኒሻንጉል ክልል ጉባ ወረዳ  እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በትልቅነቱ በአፍሪካ ቀዳሚና በዓለም ደግሞ ስምንተኛ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም