ቀጥታ፡

በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ዛሬ ሌሊቱን በዘረፋ ላይ የነበሩ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መጋቢት 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ሌሊቱን ነዋሪዎችን በመሳሪያ በማስፈራራት ዘረፋ ሲፈፅሙ የነበሩ አንድ የክልሉ ልዩ ሃይል አባልን ጨምሮ 7 የሽፍታ ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ።

በከተማዋ በተለምዶ ቻይና ካምፕ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ታጣቂዎቹ ዛሬ ሌሊቱን እየተዘዋወሩ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን በመደብደብና በመሳሪያ በማስፈራራት ዘረፋ ፈፅመዋል።

የወንጀል ድርጊቱን የፈፀሙት አንድ የክልሉ ልዩ ሃይል አባልን ጨምሮ 7 የሽፍታ ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ ለኢዜአ እንደገለጹት፤

ታጣቂዎቹ የነዋሪዎችን በር በሃይል በመደብደብና በመሳሪያ በማስፈራራት ገንዘብ ሲቀበሉ ከነዋሪዎች በተሰጠ ጥቆማ በመከላከያ ሰራዊቱ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።

ኮማንድ ፖስቱ በወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉትን ሽፍቶች ጉዳይ እያጣራ መሆኑንም ገልጸዋል። በትናንትናው ዕለት በዞኑ ማንዱራ ወረዳ በሽፍቶች ጥቃት የሰባት ንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን አስታውሰው፤ "መከላከያ ሰራዊቱ ወንጀለኞቹን የማደን ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም