መሥዋዕትነት እየከፈልንም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን ጉዟችንን እንቀጥላለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ - ኢዜአ አማርኛ
መሥዋዕትነት እየከፈልንም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን ጉዟችንን እንቀጥላለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
አዲስ አበባ መጋቢት 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) “መሥዋዕትነት እየከፈልንም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን ጉዟችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ወለጋ ዞን በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።
“የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን ለሟች ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እንገልጻለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ዓለማችን በወረርሽኝ ተጨንቃ መፍትሔ በምትፈልግበት በዚህ ሰዓት፣ ሆን ብለው በሰዎች ላይ መከራና ስቃይ የሚጨምሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች በምንፈልጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ስፍራ የላቸውም” ብለዋል።
“ጠላቶቻችን በውስጥና በውጭ ተደራጅተው ንጹሐን ዜጎቻችንን በመግደል የጀመርነውን ጉዞ ለማሸማቀቅና ከመንገዳችን ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
“መሥዋዕትነት እየከፈልንም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን ጉዟችንን እንቀጥላለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሁሉም ቦታ በደረሰው ጥቃት አጸፋ እርምጃ በክልልና በፈዴራል መንግሥት ቅንጅት እየተወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ጥፋት ኃይሎች ወጥመድ ላለመውደቅ በማስተዋል እየተጓዘ፤ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ጥፋተኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብ እና እንደዚህ ዓይነት ግድያዎች ፈጽመው እንዲቆሙ በትብብር ልንሠራ ይገባል።
ኢትዮጵያ በመሥዋዕትነት የቆመች፤ በመሥዋዕትነት የምትቀጥል ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ “በትብብርና በአንድነት መንፈስ የኢትዮጵያን ጠላቶች ደግመው እንዳይነሡ አድርገን ማጥፋት አለብን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።