በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የሚተከል 730 ሚሊዮን የዛፍ ችግኝ እየተዘጋጀ ነው -የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ

83

ሀዋሳ መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ) በመጭው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የሚተከል 730 ሚሊዮን የዛፍ ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን የደቡብ ክልል አካባቢ ጥበቃ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ግጄ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኙ እየተዘጋጀ ያለው በመንግስትና በማህበር በተቋቋሙ ጣቢያዎች ነው።

ለችግኝ ተከላው የሚሆን ቦታም እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግኞቹን በ141 ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል በእቅድ መያዙን አመልክተዋል።

"የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማትን የምናስፈጽመው ካለፉት ዓመታት ልምድ በመነሳት ነው" ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ በተለይ ችግኞቹ የፅድቀት መጠናቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ሙሉ የዕድገት ደረጃቸውን እንዲከተሉ የማፍላት ሥራው ቀደም ተብሎ መጀመሩን ተናግረዋል።

በዝግጅት ላይ ካሉ ችግኞች ውሰጥ 40 በመቶው ለግንባታ፣ 30 በመቶው ለማገዶ የሚውሉና በፍጥነት የሚደርሱ የዛፍ አይነቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"ቀሪ 30 በመቶ ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት የሚውሉ ሀገር በቀል የዛፍ አይነቶች ናቸው" ብለዋል።

እንደ አቶ ግዛቴ ገለፃ የችግኝ ተከላው ከሚያዚያ እስከ ነሀሴ 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በህዝብ ተሳትፎ ከተተከሉ 1 ቢሊዮን ችግኞኝ  ውሰጥ  84 በመቶ  መጽደቁን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም