ቀጥታ፡

ኦነግ ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን 28 ንጹሃን ዜጎች መግደሉን የኦሮሚያ ፖሊስ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22/2013 ( ኢዜአ) ኦነግ ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ 28 ንጹሃን ዜጎችን ገድሎ 12 ማቁሰሉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ በሰጠበት ወቅት በዞኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ በደረሰው አሰቃቂ ግድያ የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ እንደሚሉት የጥፋት ቡድኑ ስልጣንን በኃይል ለመያዝ በማሰብ አሰቃቂ ግድያዎችን በዜጎች ላይ እየፈጸመ ይገኛል።

በትናንትናው እለትም በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት 50 የሚሆኑ ዜጎችን አንድ ላይ ሰብስቦ ያለ ርህራሄ በእሩምታ ተኩስ 28 ሰዎችን ገድሏል ነው ያሉት።

ከሟቾች መካከል 16 ወንዶችና 12 ሴቶች ሲሆኑ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጨምሮ የሌሎች ብሔሮች ተወላጆችም ይገኙበታል ብለዋል።

የክልሉ ፖሊስም ትናንት ከምሽቱ አራት ሰዓት ጀምሮ ለአንድ ሰዓት ያህል ተጉዞ በስፍራው የደረሰ ሲሆን ሶስት ታጣቂዎችን የገደለ ሲሆን የቀሩት ላይ አሰሳ እያደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።

የክልሉ ፖሊስ ጥቃቱ የተፈጸመበት ስፍራ ሲደርስም የሟቾችን አስከሬን እንዲነሳ ያደረገና ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 12 ሰዎችም ህክምና እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል ኮሚሽነር አራርሳ።

ባለፈው አንድ ዓመት በጥፋት ቡድኑ ኦነግ ሸኔ ላይ በጸጥታ አካላት በተወሰደ ጥቃት 2 ሺህ 600 የሚሆኑት እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 947 የቡድኑ አባላት የተገደሉ ሲሆን 489 የተማረኩና 107 ደግሞ እጅ የሰጡ የቡድኑ አባላት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽነር አራርሳ አክለውም በጥፋት ቡድኑ ከአንድ ዓመት በላይ በሚሆን ጊዜ ውስጥ ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽነር አራርሳ ኦነግ ሸኔ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጠላት መሆኑ እንዲታወቅ በተባበረ ክንድ ቡድኑን ለማጥፋት መስራት ያስፈልጋል ይላሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ አካላት ፖሊስ ጥሪ ተደርጎለት ያልደረሰ የማስመሰል ነገር አለ፤ ይህም ትክክል አይደለም ብለዋል።

በሕብረተሰቡ በኩል ጥሪ ተደርጎለት ያልደረሰ የፖሊስ አባል ካለ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ይወሰዳልም ነው ያሉት።

እየተጋነነ የሚቀርበው የሟቹች ቁጥርም ትክክል አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ ኦነግ ሸኔ የሚያደርሰውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ህዝብ የማደራጀትና ሚሊሻ የማስታጠቅና የማሰማራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም