ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት የባህልና ፍልስፍና ለውጥ ያስፈልጋል-ምሁራን

  አዲስ አበባ መጋቢት 22/2013 (አዜአ) በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት የባህልና ፍልስፍና ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ምሁራን መከሩ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ችግሮቹ በከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደሚፈቱ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ "የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ለአገራዊ ልማትና ብልጽግና" በሚል በበየነ መረብ የታገዘ የምሁራን ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ በአሜሪካ ሜዲአሌ ኮሌጅ የሥነ-ትምህርት መምህር ፕሮፌሰር በለጠ ከበደ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአገር እድገት ያበረከቱትን አስተዋጽኦና የጥራት ችግሮችን መፍትሄ በማመላከት ጽሁፍ አቅርበዋል።

ተቋማቱ ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ፣ የሰው ኃይል ፍላጎትን በማሟላት፣ ዘመናዊነትን በማስፋፋትና በአገራዊ ግንባታ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ከትምህርት ጥራት አንጻር ሥር የሰደዱ ችግርች ይስተዋሉባቸዋል ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ በጽሁፋቸው በከፍተኛ ትምህርት የተቋማት ውጤታማነት፣ አሳታፊ የመማር ማስተማር ሥነ-ዘዴ፣ የአመራር ብቃትና ተጠያቂነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ዘርዝረዋል።

ከመማር ማስተማሪያ ሥነ-ዘዴው የሚያያይዘውን በተግባር የተደገፉና አሳታፊ አለመሆናቸው ችግር ውስጥ ለአብነት ጠቅሰዋል ፕሮፌሰር በለጠ።

ተጠያቂነትን ማስፈን፣ አማራጭ ስልቶችን በጥናት መለየት፣ አሳታፊ  የመማር ማስተማር ዘዴን በመተግበር አጠቃላይ የባህልና የፍልስፍና ለውጥ እንደሚያስፈልግ በመፍትሄነት አቅርበዋል።

ለዚህም ስትራቴጂክ ባህሪን በተቋማት መዘርጋት፣ የምዘና ሥርዓትን ተግባራዊ ችሎታን እንዲፈትሽ ማድረግና ጥንካሬና ክፍተቶችን የሚገመግም ባህልና ሥርዓት ማዳበር እንደሚያስፈልግ  ምሁሩ አመላክተዋል።

እንደ ፕሮፌሰር በለጠ ገለጻ ተማሪዎች በራሳቸው ሁኔታዎችን የሚማሩበት፣ የቴክኖሎጂ ዕውቀታቸውን የሚያዳብሩበት፣ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉበት ፍልስፍናንም ማጠናከር ያስፈልጋል።

ሌላው ጽሁፍ አቅራቢ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ትምህርት አግባብነት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚሰጠው ትምህርት ከንድፈ ሃሳብ በዘለለ የማህበረሰቡን ችግር በመፍታት ክፍተት እንደሚስተዋልባቸው ገልጸዋል።

አብዛኛዎቹ የትምህርት መርሃ ግብሮች የወቅቱን ገበያ ያላገናዘቡ በመሆናቸው እንዲፈተሹም መክረዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ዳሬክተር ጄኔራል ዶክተር ኤባ ሚጄና በጥራትና አግባብነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

ፖሊሲው አሳታፊ ትምህርትን በመስጠት ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎችች ለማፍራት ያለመ ሲሆን፣ ከገበያ ፍላጎት ጋር ያልተጣጣሙ ስልጠናዎችም እንደማይሰጡ አረጋግጠዋል።

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣አገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም