ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ምርጫ በሲዳማ ክልል የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

ሀዋሳ ፤ መጋቢት 22/2013 (ኢዜአ) ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሲዳማ ክልል የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የፓርቲው የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ጉዳይ የሲዳማ ክልል ሃላፊ አቶ አስፋው ጎነሶ ለኢዜአ እንዳሉት ከሃገሪቱ ዜጎች እኩሌታ ቁጥር ያላቸውን ሴቶች የምርጫ ተሳትፎ ማጎልበት ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

ለዚህ እውን መሆን በዘንድሮው ምርጫ ሴቶች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ተሳትፎ ከነበራቸው 20 በመቶ ወደ 42 በመቶ ፣ ለክልሉ ምክር ቤት ደግሞ ከእጥፍ በላይ በማሳደግ 48 ነጥብ 9 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን አስታውቀዋል።

በትምህርት ዝግጅት፣ ባላቸው አቅም፣ የፖለቲካ አቋምና ህዝብን ለመለወጥ ያላቸው ፍላጎትና ዝግጁነት ተገምግሞ ብቁ መሆናቸው የተረጋገጡ ሴቶች ተመልምለው ለዕጩነት ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

ዕጩዎቹ በኮታ ሳይሆን ከዚህ በፊት በተመደቡበት ኃላፊነት ደረጃ ውጤታማ የነበሩና በቀጣይ ሃገሪቱ ያለመችውን የብልጽግና ጉዞ ከግብ ለማድረስ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት ተጭኖ በነበረው የጭቆና ቀንበር የተማረረው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ለማርካት ዘርፈ ብዙ ትልሞችን አንግቦ የተነሳው የለውጡ ሃይል በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል የሴቶችና ወጣቶች ሁለንተናዊነት ተሳትፎ ለማረጋገጥ መሠራት ይገባል ብለዋል።

ይህንን መሰረት በማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ሴቶችን ፖለቲካዊ ፣ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ የፓርቲውን ግብ አውቀው ለተፈጻሚነቱ እንዲተጉ ለማድረግ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ አስፋው ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አየለች ሌዳሞ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ በተለይ በፌደራል ደረጃ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ሴቶች በሀላፊነት ቦታ ከተቀመጡ አይወጡም የሚሉ እሳቤዎች የተሳሳቱ ስለመሆናቸው በብቃት ተወጥተው አስመስክረዋል ብለዋል።

የተጀመረው የለወጥ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሴቶችን ተሳትፎ በየደረጃው ለማጎልበት የሚመለከተው ሁሉ በሃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ሴቶች ጎልተው እንዲወጡና ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ ለማስቻል የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ለሴቶች በተሰጠው ትኩረት በሁሉም መስክ መብታቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማስከበር የተጀመሩት ጥረቶች መልካም መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ናቸው።

በቀጣዩ ምርጫም በውሳኔ ሰጪነት ደረጃ በቂ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ፓርቲው በሰጠው ትኩረት በርከት ያሉ ሴቶች በዕጩነት እንዲቀርቡ መደረጉ የሴቶችን ተነሳሽነት እንዲጨመር ማስቻሉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም