ለግዕዝ ትምህርት ትኩረት ባለመሰጠቱ ዕውቀቱን እየተጠቀምንበት አይደለም- የግዕዝ ቋንቋ አጥኚዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለግዕዝ ትምህርት ትኩረት ባለመሰጠቱ ዕውቀቱን እየተጠቀምንበት አይደለም- የግዕዝ ቋንቋ አጥኚዎች
አዲስ አበባ መጋቢት 22/2013 (አዜአ) ለግዕዝ ትምህርት ትኩረት ባለመሰጠቱ ከቋንቋው የሚገኘውን ዕውቀት እየተጠቀምንበት አይደለም ሲሉ የግዕዝ ቋንቋ አጥኚዎች ገለፁ።
የግዕዝ ትምህርት በአግባቡ ባለመሰጠቱም የአማርኛ ፊደላት ትርጓሜን እያዛባው ነው ብለዋል።
ግዕዝ ቀዳሚ ቋንቋ ለመሆኑ አዳም የሚለው የግዕዝ ቃል አመላካች እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስረዳሉ።
አዳም የሚለው ቃል “አደመ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ውብ፣ ያማረ፣ የተዋበ፣ ቅምጥል የሚል ትርጉም ይሰጣል።
አዳም የመጀመሪያው የሰው ፍጡር በመሆኑ ከሰው ፍጥረት ጀምሮ የግዕዝ ቋንቋ እንደነበረና ግዕዝ አዳም ከፈጣሪው ጋር እንደተነጋገረበትም ይናገራሉ።
ግዕዝ ሁለት ትርጉሞች ያሉት ሲሆን፣ በዐይኑ “ዐ”፣ “ዕ” ሲፃፍ አንደኛ የሚል ትርጉም ይሰጣል። ግእዝ በአልፋው “አ”፣ “እ” ሲፃፍ ሁለተኛ ወይም ነፃነት የሚል ትርጉም ይኖረዋል።
ግዕዝ ከፊደል ጋር ቁርኝት ስላለው ያለ ፊደል ቃል እንደማይኖርም አጥኚዎች ይገልፃሉ።
የግዕዝ ቋንቋ በአክሱም ዘመነ መንግሥት መደበኛ ቋንቋ ነበር። እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመንም ዋነኛ የመግባቢያ ቋንቋ ሆኖ አገልግሏል።
አሁን ላይ ግን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ-ስርዓትና አገልግሎት ተወስኖ እንደሚገኝ የግዕዝ ቋንቋ አጥኚና ተመራማሪው መጋቤ ጥበባት መሪጌታ ሀዲስ መሐሪ ይናገራሉ።
በቋንቋው ካለው ዕውቀት ኢትዮጵያ እንዳልተጠቀመችበት በመግለጽ ሌሎች አገሮች ከኢትዮጵያ የወሰዱትን ጥናትና ምርምር እያደረጉበትና እያስተማሩበት ናቸው ይላሉ።
የግዕዝ ቋንቋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠብቃ ብታቆየውም፤ ሌሎችም የሚጠቀሙበት አገራዊ ሀብት እንደሆነም መጋቤ ጥበባት ሀዲስ አስረድተዋል።
የፊደል ተመራማሪና ሠዓሊ አከመን ዘወልድ በበኩላቸው “ለግዕዝ ትምህርት ትኩረት ባለመሰጠቱ የፊደላት ትርጓሜ እንዲዛባ እያደረገ ነው”ብለዋል።
ፊደሎች የየራሳቸው ቁጥርና ስያሜ ያላቸው ሲሆኑ፣ተመሳሳይ ሞክሼ ፊደሎችም እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በፊደል ገበታ ላይ የሶስት ሀ፣ የሁለት ሰ፣ የሁለት አ እና የሁለት ጸ መኖር የራሱ ትርጉም እንዳለው ያስረዱት ተመራማሪው፣ ይህን ባለመገንዘብ በተመሳሳይ ፊደል ይጠቀማሉ ይላሉ።
ተመሳሳይ ፊደላት የራሳቸው ትርጓሜ አላቸው የሚሉት የፊደል ተመራማሪው ከ "ሀ" ጀምሮ እስከ "ፐ" ያሉት እያንዳንዳቸው ፊደላትም የየራሳቸው ትርጉም እንደተቀመጠላቸው ይናገራሉ።
ፊደላቱ የየራሳቸው ቁጥር እንደተወከሉላቸውም የፊደል ተመራማሪው ይናገራሉ።
ሊቃውንት በፊደልና በግዕዝ ቋንቋ ላይ ያተኮሩ መጻሕፍት ቢያሳትሙ ለውጥ እንደሚመጣም እምነት አላቸው።
የባህልና ቱሪዝም እና የትምህርት ሚኒስቴሮች እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ፊደላትን በማስተማርና የግዕዝ ቋንቋ ተጠብቆ እንዲቀጥል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የፊደልና የግዕዝ ቋንቋ ምንጭ ከኢትዮጵያ የተገኘ ሲሆን፤ የአማርኛና የትግርኛ ቋንቋዎችም በግዕዝ ቋንቋ መነሻነት መፈጠራቸውን "የካም መታሰቢያ" የተሰኘው የአስረስ የኔሰው መጽሐፍ ያስረዳል።