ባለሀብቶችን በማሳተፍ ህብረተሰቡን በፍትሀዊነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ለማከናወን ይሰራል-ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
ባለሀብቶችን በማሳተፍ ህብረተሰቡን በፍትሀዊነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ለማከናወን ይሰራል-ብልጽግና ፓርቲ
ድሬዳዋ፣ መጋቢት 22/ 2013 (ኢዜአ) ብልጽግና ፓርቲ ባለሀብቶችን በማሳተፍ ህብረተሰቡን በልማት ፍትሀዊነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ለማከናወን በትጋት እንደሚሰራ የፓርቲው የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ በድሬዳዋ ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂዷል።
በፓርቲው የድሬዳዋ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት 27 አመታት ድሬዳዋ ባሏት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፀጋ ልክ ሳትለማ ቆይታለች።
ድሬዳዋ ሀገሪቱን ከጎረቤት ጂቡቲ የሚያገናኙ ዘመናዊና የጥንት የባቡር ሀዲድ መስመር፣ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ የክፍያ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ባለቤት መሆኗን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ለሲሚንቶና ለሌሎች ኢንዱስትሪ ምርቶች በግብአትነት የሚያገለግሉ ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች መገኛ መሆኗንም አመልክተዋል።
ከተማዋ ያሏት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ጸጋዎች በትክክል ልማት ላይ እንዲውሉ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡
የተጀመረው ዘመናዊ የደረቅ ወደብ ግንባታም እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው ከተማዋ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶችና መሰረተ ልማቶች በመጠቀም በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ባለሀብቶችን በስፋት በማሳተፍ ህብረተሰቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል ።
ከተማዋን ለኑሮ ተመራጭና የምስራቅ አፍሪካ የኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከል እንድትሆን ፓርቲው ስትራቴጂ ዘርግቶ ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
"በከተማዋ ነዋሪዎቿ ከልማቱ በእኩልነትና በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፓርቲው በቁርጠኝነት ይሰራል" ብለዋል፡፡
ፓርቲው በዘንድሮ 6ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ካሸነፈ የድሬዳዋ የሥራ ቋንቋዎች አማርኛ፣ ኦሮሚኛና ሱማሌኛ እንደሚሆኑ የገለጹት ደግሞ የፓርቲው ምክትል ኃላፊ ሼህ ኡስማን አህመድ ናቸው፡፡
ምክትል ሀላፊው በማከል "ድሬዳዋን የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መናኃሪያ በማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ነዋሪዎቿ በእኩልነትና በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል" ብለዋል፡፡
"በአስተዳደሩ በገጠር ቀበሌዎች አነስተኛ የመስኖ ተቋማትና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ህብረተሰቡ በቀላሉ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ይሰራል" ሲሉም አመላክተዋል።
ፓርቲው በከተማዋ ለማከናወን ላቀዳቸው የልማት ውጥኖች ተግባራዊነት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሀላፊ አስታውቀዋል።
የፓርቲው አባላትና አመራሮች በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች በመዘዋወር የፓርቲውን የልማት -መርሃ ግብሮች ያስተዋወቁበትና የምረጡን ቅስቀሳ ያደረጉበትን ስነ ስርአት ዛሬ አካሂደዋል።