ምርጫው አገራዊ አንድነትን እንዲያጠናክርና ዴሞክራሲያዊነቱን እንዲጠብቅ በኃላፊነት ሊሰራ ይገባል- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው አገራዊ አንድነትን እንዲያጠናክርና ዴሞክራሲያዊነቱን እንዲጠብቅ በኃላፊነት ሊሰራ ይገባል- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ መጋቢት 22/2013 (አዜአ) ምርጫው አገራዊ አንድነትን እንዲያጠናክርና ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊቱን ጠብቆ እንዲካሄድ በኃላፊነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ለስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሁለት ወራት ገደማ የቀሩት ሲሆን፤ ምርጫውን ለማከናወን ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ ''ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንፈልጋለን። ይህን ለማሳካትም የበኩላችንን እየሰራን እንገኛለን''ብለዋል።
''ገዢ ፓርቲ እንደመሆናችን ድርብ ኃላፊነት ለመወጣት እየሰራን ነው'' ያሉት ኃላፊው የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን የጸጥታ ኮሚቴ ከማቋቋም ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው ምርጫ ካለፉት ጊዜያት ምርጫዎች በአሳታፊነቱ፣ በዴሞክራሲያዊነቱና በፍትሃዊነቱ የተሻለ ለማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ይህንኑ ያመላክታል ብለዋል።
ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ግን የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል።
የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው በአገሪቱ የፖለቲካ ትግል መካሄድ ያለበት በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆን አለበት ይላሉ።
ለዚህም ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን መሥራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
ገዥው ፓርቲም ያለበትን ኃላፊነት በመገንዘብ በአዲስ የአሰራር መንፈስ ለምርጫው ሰላማዊነት ሊሰራ ይገባዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የብሄራዊ ምርጫ ኮሚቴ የዋና ዋና የሚዲያዎች አስተባባሪ ወይዘሮ ትዕግሥት ወርቅነህ ሁሉም የምርጫው ተሳታፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫ ቦርድና መንግሥት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በዚህም ፓርቲያቸውም የምርጫው ሂደት በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ለአባላትና ለደጋፊዎቻቸው የሚንቀሳቀሱበትን መለያ እንዳዘጋጀ አንስተዋል።
ለስድስተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የዘንድሮው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል።