''ሐኪም መሆን መታደል ነው፤ ሐኪም ሆኖ ደግ መሆን ደግሞ ትልቅ መታደል ነው'' - ኢዜአ አማርኛ
''ሐኪም መሆን መታደል ነው፤ ሐኪም ሆኖ ደግ መሆን ደግሞ ትልቅ መታደል ነው''

አዲስ አበባ መጋቢት 22/2013 (አዜአ) ''ሐኪም መሆን መታደል ነው፤ ሐኪም ሆኖ ደግ መሆን ደግሞ ትልቅ መታደል ነው'' - ይህ የተባለው ዓለም አቀፉ የሐኪሞች ቀን ትናንት በተከበረበት ወቅት ነው፡
የዓለም የሐኪሞች ቀን ማርች 30 የሰዎችን ህይወት ለመታደግ የሚጥሩ ባለሙያዎችን በመዘከር ይከበራል።
ቀኑን አስመልክቶ ለዓመታት ታካሚዎቻቸውን በቅንነትና በታጋሽነት እያገለገሉ የሚገኙት ዶክተር ዳዊት በሬሳ በታካሚዎቻቸው፤ በስራ ባልደረቦቻቸውና በአብሮ አደጎቻቸው በብሔራዊ ቲያትር የምስጋና ዝግጅት ተከናውኖላቸዋል።
የዶክተር ዳዊት በሬሳ ተመላላሽ ታካሚ የሆኑት ወይዘሮ ዘለቃ ምስለዓለም "ዶክተር ዳዊት ሐኪም ብቻ ሳይሆን ለእኔና ለቤተሰቦቼ ከአምላክ የተሰጠን በረከታችን ነው" ብለዋል።
ላለፋት 15 ዓመታት በዶክተር ዳዊት የህክምና ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጸው በዚህ ወቅት ችግራቸውን በመረዳት አስፈላጊውን እገዛ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአገሪቱ ዶክተር ዳዊትን የመሰሉ በርካታ የህክምና ባለሙያዎች ተበራክተው የተቸገሩትን መርዳት ቢችሉ ብዙ ታካሚዎችን ከሞትና ከከፋ ችግር ማዳን ይቻላል ሲሉም ገልጸዋል ።
ዶክተር ዳዊት ታካሚውን በደግነትና በትህትና በማስተናገድ ወደ ሙሉ ጤና እንዲመለስ የሚያደርገውን እንክብካቤና ድጋፍ ሁሉም የህክምና ባለሙያ ሊማርበት ይገባል ሲሉ የፒያሳ አካባቢ ነዋሩ የሆኑት አቶ ልዑል መንበረ ተናግረዋል።
በምስጋና ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት በጤና ሚኒስቴር የጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል እንደገለጹት፤ ሐኪሞች ለታካሚዎቻቸው ሁሉ ነገራቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ሲሆኑ ታካሚዎች ደግሞ ራሳቸውን ከፈጣሪ በታች እምነት በመጣል የሚሰጧቸው ናቸው።
በአለም ላይ ቀኑን አስመልክቶ ለሐኪሞች ምስጋና መስጠት የተለመደ መሆኑን በማስታወስ በአገሪቱ ይህ በጎ ሃሳብ መጀመሩ ለባለሙያዎቹ ትልቅ ጉልበት ይሆናል ብለዋል።
ቀኑን በማስመልከት የተዘጋጀው የምስጋና ፕሮግራም ወጣት ሐኪሞች ተግባሩን አርዓያ በማድረግ ማህበረሰቡን በቅንነትና በታጋሽነት እንዲያገለግሉ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
''ሐኪም መሆን መታደል ነው ሐኪም ሆኖ ደግ መሆን ደግሞ ትልቅ መታደል ነው'' ብለዋል።
ለዶክተር ዳዊት ብዙ ችግር ያለባቸውን ታካሚዎች ማቅረብ፣ መንከባከብ፣ በገንዘብና በዕውቀት ማገልገል መገለጫዎቹ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ዶክተር ዳዊት በሬሳ በበኩላቸው የተደረገላቸው የምስጋና ዝግጅት ያልጠበቁት መሆኑን በመናገር ሁሉንም አመስግነዋል።
ህክምና ማለት የአንድን ሰው በሽታ በማወቅ መፍትሄ መስጠት ብቻ አለመሆኑን በትምህርት ዓለም መማራቸውን አስታውሰው አብዛኛውን ጊዜ ከአካላዊ ህመም ባሻገር ከስነ ልቦና ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች አሉ ብለዋል፡፡
ይህን ተከትሎ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች መድሃኒት የመግዛት አቅም እንደማይኖራቸውና ውስጣቸው እንደሚጎዳ ገልጸዋል።
በዚህም ማንኛውም የህክምና ባለሙያ እውቅቱን ተጠቅሞ በሽታን ከማከም ባለፈ የታካሚውን የተጎዳ ስነ ልቦና በመንከባከብ፣ በማጽናናትና በመደገፍ ከሸኘ ያን ጊዜ ታካሚው ትክክለኛ ህክምና አገኘ ማለት እንደሚቻል ገልጸዋል።
ስራቸውን ለረጅም ዓመታት በዚህ መልኩ ሲያከናውኑ በመቆየታቸው ጥሩ ስሜት እንደሚሰማቸው ገልጸው ፤ የምስጋና ፕሮግራሙ ወደፊት ትልቅ ስራ እንድሰራ አበረታቶኛል ብለዋል።
ወደፊት አቅም የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ ባለሃብቱን በማስተባበር የተለየዩ ስራዎችን ለመስራት ከጓደኞቻቻው ጋር እየመከሩ መሆኑን ገልጸዋል።