በኢትዮጵያ ከመደበኛ ተቋማት ጋር ባህላዊ እሴቶችን በማሰናሰል ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደሚቻል ምሁራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከመደበኛ ተቋማት ጋር ባህላዊ እሴቶችን በማሰናሰል ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደሚቻል ምሁራን ተናገሩ
አዲስ አበባ መጋቢት 21/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከመደበኛ ተቋማት ጋር ባህላዊ እሴቶችን በማሰናሰል ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደሚቻል ምሁራን ተናገሩ።
የአዲስ ወግ ወርሃዊ ውይይት "ሰላምና ደህንነት በምርጫ ወቅት" በሚል ሐሳብ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።
በመጭው ግንቦት የሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል።
ይህም በኢትዮጵያ ቀደም ሲል በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች የነበረው ግጭትና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይደገም ካለ ፍላጎት የመነጨ ነው።
የምርጫውን ሰላማዊነት አስመልክቶ በአዲስ ወግ የውይይት መድረክ የተነሳው ሐሳብም ይህን የሚደግፍ ነው።
በተለይ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችና የሰላም ግንባታ እሴቶች በመደበኛ ተቋማት ላይ ተግባራዊ ቢደረጉ የምርጫው ውጤት ከግጭት ይልቅ ሰላማዊነቱ የጎላ እንደሚሆን ነው የተገለጸው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ የሚታወቁት ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የኤስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰርና የሰላም ሚኒስትር አማካሪው ዶክተር ሳሙኤል ተፈሪ የውይይት መነሻ ሐሳብ አቅርበዋል።
ዶክተር ሳሙኤል እንደሚሉት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ ጠንካራ ባህላዊ እሴቶች ይገኛሉ።
በመሆኑም ከመደበኛ ተቋማት ጋር ባህላዊ እሴቶችን በማሰናሰል ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደሚቻል ይናገራሉ።
በተለይ ምርጫን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቶችን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድርግ ላቅ ያለ ሚና አላቸው ብለዋል።
ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ በበኩላቸው በየአካባቢው ያሉ ባህላዊ እሴቶች ግጭቶችን ቀድሞ በመከላከልና የህብረተሰቡን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከባህላዊ እሴቶቹ በላይ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ዋነኛ ኃላፊነት ያለበት መንግስት ነው ይላሉ።
አገራዊ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ በተጻፈም ሆነ ባልተጻፈ ስርዓት ሊገዛ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ጀማሪ እንደመሆኗ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን በተለይ ከቅድመ እስከ ድህረ-ምርጫ ያሉት ሂደቶች ሰላማዊነት እንዲረጋገጥ መንግስት እየታዩ ያሉ የግጭት አዝማሚያዎችን አስቀድሞ መፍታት አለበት ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቅድመና ድህረ-ምርጫ ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ ተቋማት የማይናቅ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።
እነዚህን እሴቶች ወደ መደበኛ ተቋማት በማምጣት ማስተዋወቅና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተአማኒነትም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያነሱት።