ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የፈረስ ቆዳ ቁስለት በሽታ ፈዋሽ መድሀኒት በምርምር ማግኘቱን ይፋ አደረገ

ጎንደር፣ መጋቢት 21/2013 (ኢዜአ) የፈረስ ቆዳ ቁስለት በሽታ ፈዋሽ መድሀኒት በምርምር ማግኘቱን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያገኘው መድሀኒት በፈረሶች ቆዳ ላይ ቁስለት በማስረስ ከባድ ህመምና ሞት የሚያስከትል በሽታን የሚያድን መሆኑ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ፈረሶች እስከ 30 በመቶ የሚሆኑት በቆዳ ቁስለት በሽታ ተጠቂ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ቴዎድሮስ ፈንታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት  በቅመማ የተገኘው መድሃኒት በዝቅተኛና በመካከለኛ ደረጃ በበሽታው የተጠቁ ፈረሶችን ሙሉ በሙሉ ማዳን የሚያስችል ነው፡፡

በከፍተኛ ደረጃ በበሽታው የተጠቁ ፈረሶችን ሙሉ በሙሉ ለማዳን የሚያስችል ቀጣይ ምርምር እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በምርምሩ የተገኘው መድሃኒት በስድስት ሳምንት ውስጥ የማዳን አቅም እንዳለው በዝቅተኛና በመካከለኛ ደረጃ በበሽታው በተጠቁ ፈረሶች ላይ ተሞክሮ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

መድሃኒቱ ከሀገር በቀል የተፈጥሮ እጸዋቶች የተቀመመና በቅባት መልክ የሚሰጥ የምርምር ግኝት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ላለፉት ሶስት አመታት በተደረገ ምርምር የተገኘው መድሀኒት በ30 ፈረሶች ላይ ተሞክሮ ውጤቱ አስተማማኝ እንደሆነ መረጋገጡን  አብራርተዋል።

በሳይንሳዊ ስሙ "ኢፐዝዋቲክሊም ፋንጂትስ’’ በተባለ በሽታ አምጪ የፈንገስ ተሃዋሲያን የሚተላለፈው የፈረሶች የቆዳ በሽታ በአካባቢው "ንድፍት’’ተብሎ የሚጠራ እንደሆነም አመልክተዋል።

በሽታው በፈረሶች እግር፣ ደረትና አንገት አካባቢ በስፋት የሚስተዋልና ከአይንና ከአፍንጫ በሚወጣ ፈሳሽ እንዲሁም በፈረሶች የቆዳ ንክኪ የሚተላለፍ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በርካታ የፈረስ ባለቤቶች ፈረሶቻቸው በዚሁ የቆዳ በሽታ ሲጠቁ ብረት አግሎ ቆዳቸውን በመተኮስ ባህላዊ የህክምና ዘዴዎችን ለዘመናት ሲጠቀሙ እንደቆዩ ገልጸዋል፡፡

"ዩኒቨርሲቲው የመድሃኒቱን የፈጠራ ባለቤትነት መብት በማስከበርና በሀገር አቀፍ ደረጃ የማረጋገጫ ሂደቶችን እንዲያልፍ በማድረግ በመድሃኒት አምራች ድርጅቶች በኩል ለምርት እንዲበቃ ይደረጋል" ብለዋል።  

በሀገራችን የበሽታው ስርጭት 80 በመቶ አካባቢዎችን እንደሚሸፍን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት በሽታ ተመራማሪ ዶክተር መርሻ አስፋው ናቸው፡፡

የበሽታው ስርጭት ከሚስተዋልባቸው የሀገራችን አካባቢዎች መካከል የአማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች ሰፊውን ድርሻ የሚይዙ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለበሽታው ምንም አይነት የመድሃኒት አቅርቦት እንደሌለ ጠቁመው ከውጪ የሚገባው መድሃኒትም ቢሆን ዋጋው በእጅጉ ውድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በጎንደር ከተማ የቀበሌ 4 ነዋሪ የሆኑትና ላለፉት 19 አመታት በጋሪ መንዳት ስራ የተሰማሩት አቶ አዱኛ ስዩም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባገኘው አዲስ መድሃኒት በቆዳ በሽታ የተጠቃው ፈረሳቸው መዳኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካሏት ከ11 ሚሊዮን በላይ የጋማ ከብቶች ውስጥ የፈረሶች ቁጥር 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንደሚደርስ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም