በሆቴልና ቱሪዝም ሙያ ሰልጥነው በዘርፉ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ ተነገረ - ኢዜአ አማርኛ
በሆቴልና ቱሪዝም ሙያ ሰልጥነው በዘርፉ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ ተነገረ
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 በሆቴልና ቱሪዝም ሙያ ሰልጥነው በዘርፉ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች ቁጥር 33 በመቶ ብቻ መሆኑን የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው ሰባተኛው ብሄራዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ በቀረበና "በኢንዱስትሪው ላይ ያለው የሰው ኃይል ሁኔታ ምን ይመስላል?" በሚለው የዳሰሰ ጥናት ነው ይህ የተገለፀው። በኢንስቲትዩቱ የምርምርና ማማከር ባለሙያ አቶ ማዘንጊያ ሽመልስ እንደተናገሩት ጥናቱ የተካሄደው የኮከብ ደረጃ ያገኙ ሆቴሎች ካሉባቸው አምስት ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ መስተዳድር ከተመረጡ ሆቴሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ በሚገኙ የቱሪዝም ድርጅቶች ነው። በጥናቱ 130 የኮከብ ደረጃ ያገኙ ሆቴሎችና 100 የቱሪዝም ድርጅቶች ተካተዋል። በጥናቱ የተገኘው ውጤት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማራው የሰው ኃይል ውስጥ 32 ነጥብ 9 በመቶው ብቻ በዘርፉ የሰለጠነ እንደሆነ ነው የሚያሳየው። "በዘርፉ ካለው 14 ሺህ 453 የሰው ኃይል ውስጥ 4 ሺህ 752 ሰራተኞች ብቻ ናቸው በሙያው የሰለጠኑት" ያሉት አቶ ማዘንጊያ የተቀረውን ድርሻ የሚይዙት በልምድ የሚሰሩና በሙያው ቀጥተኛ የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው እንደሆኑ ያስረዳሉ። በሙያው ሰልጥነው በዘርፉ እየሰሩ ከሚገኙት ውስጥም 85 ነጥብ 6 በመቶው ከቱሪዝም ዘርፍ፤ 60 ነጥብ 9 በመቶው ከሆቴል ዘርፍ የሙያ ብቃት ምዘና ያልወሰዱ መሆናቸውንም ነው ባለሙያው የገለፁት። ይህም በዘርፉ "ልምድና ክህሎት ያለው ባለሙያ እጥረት እንዲኖር አድርጓል" ያሉት አቶ ማዘንጊያ ማሰልጠኛ ተቋማቱ በዘርፉ ካሉ ኢንዱስትሪዎች ጋር የትብብር ስልጠና በመስጠት ችግሩን ለመፍታት መረባረብ አለባቸው ብለዋል። ኢንዱስትሪው በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልገው ነባር የቱሪዝምና ሆቴል ማሰልጠኛዎች አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውና አዳዲስ ማሰልጠኛ ተቋማትም ሊስፋፉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀው ሰባተኛው ብሄራዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ "የሰለጠነና የበቃ የሰው ኃይል ልማት ለዘላቂ የቱሪዝምና የሆስፒታሊቲ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደ ሲሆን፤ በዘርፉ የሚገኙና ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል። ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀው ስድስተኛው አገር አቀፍ የቱሪዝምና የእንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ከግንቦት 5 እስከ ግንቦት 9 ቀን 2010ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ መሆኑ ይታወቃል።