በአማራ ክልል የነዳጅ አቅርቦት ችግር እየተቃለለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የነዳጅ አቅርቦት ችግር እየተቃለለ ነው
ባህርዳር፤ መጋቢት 21/2013 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ለማስተካከል በተደረገው ጥረት ችግሩ እየተቃለለ መምጣቱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ።
ከነዳጅ ማደያ ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና የዕውቅና አሰጣጥ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው በመድረኩ እንዳሉት፤ የነዳጅ ግብይቱና ስርጭቱ ቀልጣፋ እንዲሆን መሰረተ ልማት እንዲሟላ በማድረግ በኩል በትኩረት እየተሰራ ነው።
ለዚህም ባለሃብቶች የማደያ መገንቢያ ቦታ በምደባ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁንም በዚህ እድል 300 ባለሃብቶች ቦታ ተረክበው ወደ ግንባታ መግባት ችለዋል ብለዋል።
በቀጣይም ሌሎች ከ500 ያላነሱ ማደያዎችን በባለሃብቶች እንዲገነቡ በማድረግ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ከፌደራል ባለድርሻ አካል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮው የሚፈታተነውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ለማስተካከል በተደረገው ጥረት አሁን ላይ የተሻለ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በሃላፊነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
በመድረኩ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ በበኩላቸው የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለማቃለል በተደረገው ጥረት የአቅርቦት ችግሩ እተሻሻለ መጥቷል ብለዋል።
በተለይ የአቅርቦት ችግሩ እንዲፈታ ንቅናቄ ከተጀመረና ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ ከጅቡቲ ወደ ክልሉ በከፍተኛ መጠን ነዳጅ እንዲገባ በመደረጉ የነበረው የአቅርቦት ችግር እየተቃለለ መሆኑን አስረድተዋል።
ሆኖም አሁንም ሙሉ በሙሉ የተረጋጋ የነዳጅ ግብይት ስርዓት ባለመፈጠሩ የአቅርቦት ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ከፌዴራል መንግስት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለነዳጅ አቅርቦት እጥረቱ መከሰት ባለማደያዎቹ የራሳቸው ቦቴ አለመኖር እንደሆነ አመልክተው፤ችግሩ እንዲፈታም 400 ቦቴዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ እየተሰራ ነው ብለዋል።
አቅርቦቱን ከመፍታት ጎን ለጎን ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመከላከል በተደረገ ጥረት ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ 150 ሺህ 491 ሊትር ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉንም ጠቅሰዋል።
ከህገ ወጥ ንግድ ሲፈፅሙ የተገኙ 50 ማደያዎችም እንዲታሸጉ፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመስጠትና የተወሰኑትን ደግሞ ፍርድ ቤት በመክሰስ ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
''የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ችግር ውስብስብ ነው'' ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ነዳጅ ማደያዎች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ፋሲል አለባቸው ናቸው።
ለአቅርቦቱ ዋነኛው ችግር እየሆነ ያለው የነዳጅ ቦቴ ቁጥር ማነስ፣ የነዳጅ ካምፓኒዎች ፍትሃዊ ስርጭት አለማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል ።
ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታም ከቀረጥ ነፃ የነዳጅ ማደያ ባለሃብቶች ከቀረጥ ነፃ ቦቴዎችን እንዲያስገቡ መንግስት ዕድል ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
ከሰሜን ወሎ ላሊበላ ከተማ የተባበሩት ነዳጅ ማደያ ባለቤት አቶ ገንዘቡ አልበው በበኩላቸው የነዳጅ እጥረት የተከሰተው የመኪና ኪራይ ዋጋ አለመሻሻልና የነዳጅ ካምፓኒዎች ነዳጅ ባዘዙት ፍጥነት አለመላካቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ታማኝ በመሆን ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ለሚገኙ 36 የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች የዋንጫና የእውቅና ምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።